ለውጡን ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ሚና እና ሀላፊነት

2054

ዳግም መርሻ/ኢዜአ/፡-

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየታዩ ያሉ ችግሮችን አስታኮ የብዙ ዜጎችና ሚዲያዎች የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ከሰነበቱትና አሁንም በዛው መልክ ከቀጠሉት ግንባር ቀደም ጉዳዮች መካከል የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር እንዲሁም የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የጸጥታ አካላት ሚናና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ነበሩ።  በተለይ መንግስት «ጥልቅ ተሀድሶ» ብሎ የሰየመውን ንቅናቄ ካወጀበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሶማሌ ክልል፣ በጌዲኦና ጉጂ፣  በሐዋሳና በሌሎችም የደቡብ ክልል አካባቢዎች፣ በድሬዳዋ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን፣ በቡራዩ… ከተነሱት ግጭቶች ጋር ተያይዞ የሰዎች ህይወት መጥፋቱ፣ ንብረት መውደሙና በርካታ ሰዎች በመፈናቀላቸው ምክንያት በሰዎች ላይ የሚደርሰው አስከፊ ጉዳት እንዳለ ሆኖ የተጀመረውን ለውጥ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማስቀጠል ከግለሰቦች ጀምሮ በየደረጃው እስከ ጸጥታ አካለት ድረስ ያሉ ተዋናዮች ድርሻቸውን በሚፈለገው መልኩ እየተወጡና ሂደቱን እያገዙ ነው ወይ ? የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪና አጠያያቂ ከሆነ ሰነባብቷል።

አሁን ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሄድ መለስ እያሉ የሚታዩት መጥፎ ሁኔታዎች የተለያዩ አካላትን ተሳትፎ ባካተተ መልኩ መሰረታዊ መፍትሄ ሳያገኝ በዚሁ መንገድ ከቀጠለ ለብዙዎች ተስፋን የፈነጠቀው ያሁኑ ለውጥ ዳር መድረሱ አጠራጣሪ ይሆናል። ከዚህም አልፎ የሀገሪቱ ህልውናና የህዝቡ አንድነት ወደ መጥፎ ሁኔታ ሊያመራ እንደሚችል ምሁራንና ፖለቲከኞች ያስጠነቅቃሉ። በዚህም ሳያበቁ እያንዳንዱ ዜጋና የሚመለከታቸው አካላት እነዚህ ችግሮች ተወግደው የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የቤት ስራቸውን ወስደው መስራት እንዳለባቸው እየወተወቱ የሚገኙበት ወቅት ነው። ከእዚህ አኳያ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዩች የህዝቡ፣ የፖለቲከኞችና የሚዲያዎች መነጋገሪያ ቢሆኑ አያስገርምም።

እንደሚታወቀው ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ አዲስ ምእራፍ ላይ ይገኛል። ባለፉት አራትና አምስት አመታት ሀገሪቱን ሊያፈራርሱና ህዝቡን ሊበትኑ የነበሩ ሁኔታዎች-የመብት ረገጣ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የህግ የበላይነት መሸርሸር፣ ስራ አጥነት፣ ኢ-ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት…ወዘተ ችግሮች ጫፍ እየደረሱ በመሄዳቸው በውስጥና በውጭ የሚገኙ የለውጥ ሀይሎች ያደረጉት መጠነ ሰፊ ትግልና ግፊት ፍሬ አፍርቶ አሁን ላይ ብዙ ለውጦችን ለማየት ችለናል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግንባር ቀደም መሪነት ተቀጣጥሎ የተጀመረው አዲሱ የዲሞክራሲ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን ያስደመመ አዳዲስ ነገሮችን አስመዝግበዋል። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተፈተዋል። በውጭ ሀገር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ወደሀገራቸው መጥተው ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው (ፓርላማው በሽብርተኝነት ፈርጇቸው የነበሩ ፓርቲዎችንና አክቲቪስቶችን ጨምሮ) ወደሀገር ውስጥ ገብተው በሰላም መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

የህግ ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው ነባር ህጎችን የማሻሻልና የመለወጥ ሂደት ተጀምሯል። ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የነበረው የሻከረ ግኑኝነት ተወግዶ ከኤርትራ መንግስት ጋር ጤነኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችና ስምምነቶች ተጀምረዋል። የህዝብ ለህዝብ ግኙንነቶችም በአዲስ መልክ እንዲጀመሩ ተደርጓል። በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተደረሱ ግኙንነቶች ወደተግባር ሲቀየሩ የሁለቱንም ሀገሮች ልማትና እድገት ለማፋጠን ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል።

በአጠቃላይ በለውጡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ወደፊት ህዝቡ የሚጠብቃቸው ብዙ ስራዎች እንዳሉ ግልጽ ቢሆንም እስካሁን በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ  ግን አብዛኞቹ የለውጥ ሀይሎችና ህዝቡ ደግፈውታል። ብሩህ ተስፋንም ሰንቀውበታል። የውጭ መንግስታት ዘንድም ያለው ድጋፍ ሁኔታ ከዚህ ብዙ የተለየ አይደለም። ብዙ መንግስታት ለውጡን አድንቀዋል። አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ከለውጡ ጎን ግጭትና ስርአት አልበኝነት በመስፋፋት ላይ ይገኛል። በዚህ ሳብያ ንጹሀን ዜጎች ውድ ህይወታቸውን እያጡ ነው። ለብዙ አመታት ጥረው ግረው ያፈሩት ሀብትና ንብረት በጥቂት ጊዜ ውስጥ በስርአት አልበኞች እየወደመባቸው ይገኛል። ከዚህም በላይ ዜጎች ቤተሰብ መስርተው ለረጅም አመታት ከቆዩበት አካባቢዎቸ በብሄራቸውና በማንነታቸው ምክንያት ብቻ በማፈናቀል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸው እንዲመሰቃቀል ሆኗል። በተለይ ደግሞ ህጻናቶች፣ ሴቶች፣ አዛውንቶቸና ሽማግሌዎች በእነዚህ ግጭቶችና ብጥብጦች ዋነኛ ተጠቂዎች እየሆኑ ነው። በውስጥ መፈናቀል ደረጃም ሀገራችን ከአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት  ዋነኛውን ረድፍ በመያዝ ላይ ትገኛለች። ይህ ሁሉ የስርአት አልበኝነትና የህገወጥነት ውጤት ነው።

አሁን ላይ እየተከሰቱ የሚገኙትን ችግሮች በእጅጉ ግራ አጋቢ የሚያደርጋቸው ለውጡን ከፊት ሆነው እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድና የለውጥ ቡድኑ  “መደመር”፣ “ፍቅር” እና “ይቅር ባይነት” የሚሉትን ቃላት የለውጡ መሪ ሀሳብ አድርገው እያቀነቀኑ ባለበትና ይህንንም ፍልስፍና በተለያዩ ተጨባጭ እንቅስቃሴዎች አስደግፈው እያሳዩ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው።

በመሰረቱ እነዚህ የለውጥ ሀሳቦች በውስጣቸው ሰፊ ትርጉሞችን ያቀፉ ቢሆንም በመሰረታዊነት ግን ህዝቦችን ለማቀራረብ፣ ልዩነቶችን ለማጥበብና ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠርና በሂደትም ህዝቡን ለአንድ ሀገራዊ አላማ አስተባብሮ ለማሰለፍ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ጊዜውን የሚመጥኑ እሴቶች መሆናቸውን ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ እነዚህ ድንቅ ሀሳቦች በሁሉም ስፍራ እየተነገሩ ባለበት ባሁኑ ወቅት ሞት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የየእለት ዜና መሆኑ ነገሩን ግራ አጋቢ ቢያደርገው አያስገርምም።

ከዚህ በፊት የሚፈጠሩ ግጭቶች መንስኤ በአመዛኙ ከግጦሽ ሳርና ከውሀ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ይከሰቱ የነበረ ሲሆን ችግሮቹም እንዳሁኑ ሳይባባሱ በፌዴራል መንግሰት ጣልቃ ገብነትና በሀገር ሽማግሌዎች በውይይት የሚፈታበት ሁኔታ እንደነበረ አይዘነጋም። ሆኖም ባሁኑ ወቅት የሚታዩት ግጭቶች በመነሾዋቸው ምክንያት፣ በስፋታቸውና በሚያደርሱት የጉዳት መጠን ከላይ ከተተቀሱት የግጭት አይነቶች የተለየ መልክና ባህሪ ያላቸው መሆኑ የሁሉንም ትኩረትና ቀልብ አንዲስብ አድርጓል።

በእርግጥ ባለፉት 27 አመታት ቋንቋና ብሄርን መሰረት በማድረግ ሲሰራበት የነበረው የብሄር ፌዴራሊዝም ከአንድነት ይልቅ ክልላዊነት ላይ፣ ከእኛነት ይልቅ እኔነት ላይ፣ ከሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ይልቅ ልዩነቶቻችን ላይ ትኩረት በማድረግ የጋራ እልወናችንን የሚያኮስሱ ስራዎችን እያጎላ በመምጣቱ የይገባኛል ጥያቄዎች አቆጥቅጠው መሰረት እንዲይዙ ማድረጉን መንግስትም ጭምር ይስማማበታል። ያም ሆነ ይህ የፌዴራል ስርአቱ በሂደት የተከተለው የአፈጸጸም አቅጣጫ ህዝቡ እርስ በርሱ እንዲጠራጠር፣ እንዲፋጠጥና ልክ አሁን በከፍተኛ ደረጃ ተባብሶ እንደሚታየው በሆነ ባልሆነው በግጭትና በጥላቻ እንዲዘፈቅ ያደረገው ትልቁ ገፊ ምክንያት መሆኑ ብዙ አያጠራጥርም።

በእኔ እይታ ሌላው የወቅታዊ ችግሮቻችን አባባሽ ምክንያት በቅጡ ያልዳበረው የዲሞክራሲ ባህላችንና እንደ አጠቃላይም ፖለቲካችን ነው ማለት ይቻላል። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያውያን ለዲሞክራሲና ለዘመናዊ ፖለቲለካ መደላድል የሚሆኑ ብዙ የህግ እጥረት አለብን ብÂ አላሰብም። ይነስም ይብዛ በዚህ በኩል ብዙ የምንታማ አይደለንም። ለምሳሌ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንድ ሶስተኛውን የሚሸፍነው ክፍል ስለ ለሰብአዊና ዲሞክራሲ መብቶች የሚያወሳ መሆኑ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ምን ያህል ትኩረት እንደተሰጣቸው አንድ ጥሩ ማሳያ ነው። በተጨማሪም ምን ያህሉ በእነዚህ መብቶች ይጠቀማል የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የመረጃ ነጻነት፣ የመጻፍ ነጻነት፣ የሚዲያ ነጻነት …ወዘተ ህጎች አሉን። በሌላ በኩል ያሉባቸው የማስፈጸም ክፍተቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብቶችን የሚያስከብሩና ስለመከበራቸውም  የሚከታተሉ የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና የህግ አስከባሪ ተቋማትም ተዋቅረው መገኘታቸው ሌላው በጠንካራ ጎኑ የሚወሰድ ጉዳይ ነው ።

በአንድ ሀገር ውስጥ የዲሞክራሲ እሴቶችን የሚያጐሉ ህጎች መኖርና የዲሞክራሲ ተቋማት መዘርጋት እንደ አንድ ትልቅ እርምጃ የሚታይ ቢሆንም ብቻውን ግን እንደ መጨረሻ ግብ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። የብዙ ሀሮች ልምድ እንደሚያሳየው ተግባራቸው ሲገመገም የዲሞክራሲ ባህሪያት የሌላቸውና አምባገነን መንግስታትም ጭምር ጥሩ ጥሩ የሚባሉ የሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ እሴቶችን አጉልተው የሚያንጸባርቁ ህጎች፤ ከዚህ ጎንም የዲሞክራሲ ተቋማቶች ሊኖራቸው ይችላል። ቁም ነገሩ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ዜጐች በህግ የላይነትና በዲሞክራሲ እሴቶች ዙሪያ ግንዛቤያቸው በሚገባ ሰፍቶና የማመዛዘን ብቃታቸውም ማደጉን ተከትሎ  የያዙትን እውቀትና ግንዛቤ በማህበራዊ ግኑኝነታቸውና አኗኗራቸው ውስጥ በተጨባጭ መተግበር መቻላቸው ነው።

ይሁን እንጂ ባለፉት አመታት ይህንን በተመለከተ በሀገራችን በተለይም ከዋና ዋና ከተሞች ወጣ ባሉ አካባቢዎች ጠንካራና ተከታታይ የሆነ ስነዜጋ ትምህርት ህዝብ ውስጥ ተገብቶ ያለመሰራቱ፣ ከዚህ በተጓዳኝም ጠንካራና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የዲሞክራሲ፣ የፍትህና የጸጥታ ተቋማትን በሚፈለገው ደረጃ መገንባት ያለመቻላችን ተደማምረው አሁን እያጋጠሙን ላሉት ችግሮች ተጨማሪ መንስኤዎች ሆነዋል የሚል እምነት አለኝ። በኛ ሀገር ሁኔታ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች ግዴታቸውን እንደ መብታቸው አላወቁም። ነጻነት ሲባል የፈለጉትን ማድረግና ግዴታ እንደሌለው አድርገው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው።

ለዚህም ነው ባሁኑ ወቅት ቢያንስ ቢያንስ ለብዙ ዘመናት በታሪክ ተገንብቶ የቆየው የኢትዮጵያውያን የመቻቻል፣ የመረዳዳት፣ የመተዛዘንና የመዋደድ አኩሪ እሴቶቻችንን ወደ ጎን በመግፋት ህገ መንግስቱ ለዜጐች ያረጋገጠውን መብቶች (በዋናነትም በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብትና በፈለጉበት አካባቢ ተዘዋውሮ የመስራትና ሀብት የማፍራት መብት) በአስከፊ ሁኔታ እስከመጣስ የተደረሰውና የመኖር ዋስትናቸው ለከፋ አደጋ እየተጋለጠ የሚገኘው።

እላይ የተጠቃቀሱት ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ለውጡ ያላስደሰታቸው ወይንም ደግሞ ጥቅማቸው የተነካባቸው የጸረ ለወጥ ቡድኖች የሉም ማለት አይቻልም። እንዲያውም አሁን ላይ እየተከሰቱ ከሚገኙት ቀውሶች በስተጀርባ እነዚህ ቡድኖች አንዱ ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር እንዲጋጭ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ መልክና ገጽታ ያላቸውን አሻጥሮች ስራ ላይ በማዋል ለውጡን ለማደናቀፍና ለመቀልበስ ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ እንዳሉ መንግስትም ጭምር ያመነው ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ ግጭቶች እየተባባሱ መታየት የጀመሩት በመንግስት ደረጃ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ መሆኑ ሲታይ ለውጡን የማይፈልጉና ያልተደሰቱ የጸረ ለወጥ ቡድኖች እኩይ ሴራ መኖሩም ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

ይህ የጸረ ለውጥ ቡድን በስሜት የሚነዳ፣ ስለዲሞክራሲና የህግ የበላይነት እሴቶች በቂ ግንዛቤ የሌለው፣ አእምሮው በሀሰት ፕሮፓጋንዳ የተሞላ፣ እውነተኛና ሀሰተኛ መረጃዎችን በቅጡ መርምሮ ሀቁ ላይ መድረስ የማይችል (ለመመርመር ግድ የሌለው) ግለሰቦችን (በተለይም ደግሞ ወጣቱን) እንደጥሩ መሳሪያ አድርጎ መጠቀምን የሚመርጥ ነው።

በፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች(የመብት ተሟጋቾች) በሚባሉትም ዘንድ የተጀመረውን ለውጥ ከመደገፍና የበኩልን ከመወጣት አኳያ እስካሁን የታየው እንቅስቃሴም የመያመረቃ ነው የሚባል እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። እንዲያውም ከዚህ ይልቅ እነዚህ ቡድኖች ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት የሚጠይቀውን ጨዋነትና ስነምግባር መያዝ አቅቷቸው በተለያዩ ሚዲያዎችና በፌሰቡክ የእርስ በርስ ክስና መወነጃጀል ላይ ተጠምደው ሰላም፣ መረጋጋትና የሰከነ አካሄድ የሚፈልገውን የለውጥ ሂደት አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ለመረበሽ ሲሞክሩ ለመታዘብ የቻልንበት ሁኔታ ጥቂት የሚባል አይደለም። ይባስ ብሎም ጊዜውን የማይመጥኑና ከተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር የማይሄዱ አጀንዳዎችን እያራገቡ ህብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን ለጸብና ለብጥበጥ ሲጋብዙት ተስተውለዋል።

በአጠቃላይ አሁን ያለው ሀገራዊ ሁኔታ ሲታይ ተስፋዎችም ስጋቶችም የተደበላለቁበት ነው ማለት ይቻላል። በአንድ በኩል የተስፋና የለውጥ ሂደቱ በብዙ ወገኖች ድጋፍ ያገኘ ከመሆኑ ጎን ለጎን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀላል ግምት የማይሰጣቸውን ውጤቶች የመመዝገባቸውን ያህል በሌላ ጎኑ ለውጡን ተንተርሶ በስፋት እየታዩ ያሉት ግጭቶችና ብጥብጦች ለውጡን በማደናቀፍ ዳር እንዳይደርስ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆን ወይ? የሚለው ስጋትና ጥያቄም አብሮ ይነሳል።

ያሁኑን ለውጥ እንዲመጣ ባለፉት አመታት በውስጥም በውጭም የሚገኙ ዜጎች ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። ውድ ህይወታቸውንም አሳልፈው ሰጥተዋል።  በዚህ መልኩ የመጣውን ለውጥ እንዲደናቀፍና እንዲቀለበስ የሚሹ ጥቂቶች መኖራቸውን መካድ ባይቻልም አብዛኛው ህዝብ ግን ብዙ የህይወት መስእዋትነት ተከፍሎበት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ይሰራል የሚል አንዳችም አሳማኝ ምክንያት አይገኝም። ህዝቡ ለውጡን የሚፈልግና የሚደግፍ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይቷል። ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ሁኔታ ከለውጡ ሀይሎች ጉልእ የሆነ በተግባር ላይ የተመሰረተ በቂ ድጋፍና ተሳትፎ ታይቷል ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ አልታይም የሚል ይሆናል።

ይህ ከግምት ውስጥ ሲገባ የህዝብ ድጋፍና የለውጥ ፍላጎት በነቃ ተሳትፎና ተግባራዊ አንቅስቃሴ ማስደገፍ እጅግ ወሳኝ ነገር መሆኑ አያጠያይቅም። እናም የህግ አስከባሪ የመንግስት አካላት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ምሁራን፣ ሲቪል ማህበራት፣ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች…ወዘተ የቤት ስራቸውን በመውሰድ በተጨባጭ የሚገለጽ ድጋፍ መስጠት አለባቸው። ይህ ድጋፍ እንደሁኔታው ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ… መልክና ይዘት ያለው ሊሆን ይችላል።

በዚህ ረገድ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ ብሎም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከማድረግ አኳያ ቀዳሚና ከምንጊዜውም የበለጠ ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው። የማንኛውም መንግሰት ዋነኛ ተግባር የህዝብ ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ ነው። መንግስት ይህንን ተግባሩን ባግባቡ የማይወጣ ከሆነ የመንግስት መኖር ዋጋና ትርጉም አይኖረውም። በመሆኑም መንግስት ከጸጥታ ማስከበር ስራው በተጓዳኝ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የመንሳት ሂደት ለመግታት የመጫወቻ ሜዳው እስከምን ድረስ እንደሆነ ቀይ መስመሩን አስምሮ ማሳየት፤ ይህንንም ለህዝብ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

በመሰረቱ ግጭቶችና ብጥብጦች በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት ሲከሰቱ ይታያል። ሌላው ቀርቶ በዲሞክራሲ ባደጉት ምእራባውያን ሀገራትም ከምርጫ ጋርም ሆነ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ የተለያዩ ግጭቶችና ውዝግቦች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ይሁንና በኛ ሀገር ሁኔታ እንደሚታየው እነርሱ ጋር ችግሮቹ የከፋ ጥፋት ሳያደርሱ የመቆጣጠር አቅምና ችሎታ ስላላቸው የእለት ተእለት ኑሯቸው አደጋ ላይ አይወድቅም። በንደፈ ሀሳብም ሆነ የእነዚህ ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው በማኝኛውም ሁኔታ ውስጥ አንድን ሀገር  እንደ ሀገር መቀጠል ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል  የጸጥታ ሀይሉና ሲቪል ሰርቪሱ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ተቋማት መንግስታት ቢወጡም ሆነ ቢወርዱ፣ አንዱ ሂዶ ሌላው ቢመጣም ሆነ ሌላ አደጋ ቢከሰት  ከወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታዎቸ ጋር የማይቀያየሩ በመሆኑ ሕይወት አደጋ ላይ ሲወድቅ አይታይም።

በሌላ በኩል የጸጥታ ሀይሎች አደጋ ሲፈጠር በቸልተኝነት ቆመው የሚያዩ ከሆነ የዜጎች ሰላምና ደህንነት በእጅጉ አደጋ ላይ ነው ማለት ይቻላል። በነገራችን ላይ ግጭትን ከሚያባብሱት ነገሮች አንዱ ይህ የጸጥታ አካላት ወንጀል ሲፈጸም ዝም ብለው ማየታቸው ወይም ደግሞ ችግሩን ለማብረድ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ ያለመቻላቸው ሁኔታ ወይንም ደግሞ የቁርጠኝነት ማነስ ነው። ይህ እንደ ሀገር ትልቅ ውድቀት ነው። መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ይህን መለየትና መቆጣጠር አለባቸው። ከዚህ ጎን ለጎንም የህዝቡን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ ያልፈለጉ፣ ያልቻሉና ዝምታን የመረጡ የፖሊስና የጸጥታ አካላትም በጥንቃቄ እየተለዩ ወደ ህግ የማቅረብ ስራ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል። በመካከለኛና በረጅም ጊዜ መሰራት ያለበት ነገር ግን ከጊዜው የፖለቲካ አየር ጋር የማይወዛወዙ ፕሮፌሽናል የጸጥታና የፖሊስ አካላትን መገንባትና ከዚህ በትይዩም ተከታታይ ስልጠናችን በመስጠት አቅማቸውን ማሳደግ ነው። ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ የግጭቶቹ ምንጭ ምንድን ነው? አሁን ለምን ተባባሱ? ግጭችን ለመከላከልና ለመፍታት የተቋቋሙት የፌዴራል ተቋማትና በየክልሉ የተደራጁት የሰላም ኮሚቴዎች ለምን ውጤታማ መሆን አልቻሉም? መፍትሄው ምንድነው?…ለሚሉት ጥያቄዎች ጥልቅ የሆነ ጥናትና ፍተሻ ማካሄድ “አሳውን ለማጥፋት ኩሬውን ማድረቅ” እንደሚባለው ዋናውን ችግር ለይቶ ለማውጣትና ወደ መፍትሄው ለመድረስ ወሳኝና ጠቃሚ ነገር  መሆኑን ነው።

አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ባለማገናዘብ ፖለቲካ እናውቃለን የሚሉና አሉታዊ ውጤቶችን የሚያስከትሉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከተጠመዱት ተዋንያኖች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና አክቲቪስቶች (የመብት ተሟጋቾች) እንደሚገኙበት ቀደም ብሎ ለመጥቀስ ተሞክሯል። በእኔ እምነት እነዚህ ሀይሎች ባሀኑ ጊዜ ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ልዩነቶችን ማራገብ ላይ ሳይሆን ሀገርና ህዝብን ማረጋጋትና ሂደቱን የመደገፍ ስራ ላይ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሚኖረው መጀመሪያ ሀገር ሲኖር ነውና። ሌሎች አጀንዳዎችና ጥያቄዎች ሀገር ከተረጋጋ በኃላ ቀጥሎ ሊመጣ ይችላል። ደግሞም ለእነርሱም ቢሆን የሚሻለው የተጀመረውን የለውጥ ሂደት መደገፍና ወደፊት እንዲራመድ የማድረግ ስራ መስራት ነው። ከእዚህ ውጪ ያለው አማራጭ መጠፋፋትን የሚጋብዝ መንገድ ነው። አሁን እዛ ቋፍ ላይ ነው ያለነው ማለት ይቻላል። ይህ ደግሞ ለህዝብም ሆነ ለሀገር ጠብ የሚል ፋይዳ የለውም። የሚበጀው ነገር ህዝብን (ደጋፊዎቻቸውን) ማረጋጋት፣ ማስተማር፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር ጠለቅ ያለ ምክር መስጠትና ራሳቸውን እንዲያደራጁ ድጋፍ ማድረግ ነው።

ይህ ስራ መሆን ያለበት የእነዚህ አካላት ብቻ ሳይሆን ከእነርሱም አልፎ ወላጆችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የህዝብ አደረጃጀቶችን፣ የሲቪል ማህበራትንም ጭምር ያሳተፈ ሊሆን ይገባል። በርግጥ ባለፉት አመታት በሰብአዊ መብትና የስነ ዜጋ ትምህርት ዙሪያ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሲቪል ማህበራት በመንቀሳቀሻ ምህዳሩ መጥበብ የተነሳ ዜጎችን በማነጽና በማስተማር ስራ የሚጠበቅባቸውን ያህል ስራ ሰርተዋል ማለት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን አሁን በየገበሬ ማህበሩና በየቀየው ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የህዘብ አደረጃጀት ውስጥ የሚገኙ የሀብረተሰብ ክፍሎች …ወዘተ የጥላቻ ንግግሮችና ቅስቀሳዎች እንዳይደረጉ ቀድመው በመከላከል፣ ድርጊቶቹ ሲፈጸሙም አጥፊዎችን ነጥሎ በማውጣትና ለህግ እንዲያቀርቡ በማድረግና በችግሮች ላይ በመወያየት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

የማስተማር፣ የመምከርና አቅጣጫን የማመላከት ስራ በተለይ እንደኛ የወጣቶች ስራ አጥነት በስፋት በሚስተዋልበት ሀገር ትኩረት ሊያደረግ የሚገባው ወጣቱ ላይ ነው። ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገሮች ግጭቶችን እንደማቀጣጠያ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። በኛም ሀገር ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ወጣቱን በስሜት በመቀስቀስ ወደ ሀይል ድርጊት እንዲያመራ በማድረግ እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ይጠቀሙበታል። ይህ አሁንም ለሚታዩት አንዳንድ ግጭቶች ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህን ሁኔታ ለማረም እላይ ከተጠቀሱት አካላት በተጨማሪ ሚዲያዎችም ሊፈጠር የሚችለውን ችግር የማሳየት፣ የማስተማርና የማወያየት እንዲሁም በአጠቃላይ ህዝቡ በተጀመረው ለውጥ ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ትልቅ ሀላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል።

ምሁራንም ቢሆኑ የተጀመረውን ለውጥ ከመደገፍ አኳያ ያላቸው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባይሆንም አብዛኞቹ ምሁራን ለውጡን በሚፈለገው ደረጃ እየደገፉት ነው ማለት አይቻልም። ከዚህ አኳያ ምሁራን የህዝብ አጀንዳ ያልሆኑትን ጉዳዮች ከማራገብ፣ ተግባር ላይ መዋል ከማይችሉ ንድፈ ሀሳባዊ ትንተናዎችን ብቻ ከማቅረብና በርቀት ሆኖ ከማማት ወይንም ደግሞ አሉታዊታዊ ትችቶች ላይ ከማተኮር ራሳቸውን ማውጣት አለባቸው። ማማት የትም አያደርስም። አሁን ጊዜው ከሩቅ ሆኖ የሚተችበት ጊዜ አይደለም። በመሆኑም ምሁራኖቻችን ከዚህ ሁኔታ ውስጥ በመውጣት ህዝቡ በለውጡ ዙሪያ ተመሳሳይ ግንዛቤ፣ እምነትና ተሳትፎ እንዲኖረው የማድረግ ስራ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም እውነቱን በማሳየትና አቅጣጫ በማመላከት አቅማቸው የፈቀደውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው።

በጥቅሉ መላው የሀገሪቱ ህዝብ በለውጡና እየተከሰቱ ባሉት ችግሮች ዙሪያ ግልጽ ሆኖ የሚወያይበትና የሚነጋገርበት ጊዜው አሁን ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድም በአስራ አንደኛው የኢሀዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር ለውጡን በርቀት ሆኖ ከማድነቅ ወደ ንቁ ተሳታፊነት መሸጋገር እንደሚያስፈልግ ያሰመሩበት ጉዳይ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።

ይህ አነጋገር ቃልና አድናቆት ለብቻው ትርጉም እንደሌለውና በተግባር ላይ የተመሰረተ ድጋፍ አስፈላጊና መሰረታዊ ነገር እንደሆነ ያስገነዝባል። በመሆኑም ህዝቡ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች አማካኝነት ሲነጋገርና ሲመክር ወደ መፍትሄው እንቀርባለን። በዚህ መልኩ ስንሳተፍና የበኩላችንን ስናዋጣ ደግሞ የተጀመረው ለውጥ ዳር መድረሱና የሚፈለገውን ውጤት ማምጣቱ አያጠራጥርም።

(ትንታኔው የጸሃፊው እይታ/ትዝብት ነው)