የአይን ሞራ ግርዶሽ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የማየት ችግር መንስዔ ሆኗል፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

202
አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 የአይን ሞራ ግርዶሽ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የማየት ችግር መንስዔ እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አመለከተ። የማየት ችግር ካለባቸው 1ነጥብ5 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 600 ሺህ የሚሆኑት የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት በዓይን ሞራ ግርዶሽ እንደሆነም ተጠቁሟል። በዋናነት ለዓይን ስውርነት እያጋለጡ ያሉ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ተግባር በሚኒስቴሩ በኩል እየተከናወነ እንደሆነ ተገልጿል። ''በተለይም የትራኮማና የዓይን ሞራ ግርዶሽ በሽታዎችን ለመከላከል ከጤና ኤክስቴንሽን ጀምሮ እስከ ሚኒስቴሩ ድረስ የተቀናጀ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል'' ተብሏል። በሚኒስቴሩ የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአይን ሞራ ግርዶሽና የትራኮማ በሽታ የያዛቸው ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ካልተቻለ የዓይን ብርሃናቸውን ያጣሉ። ''በአሁኑ ወቅት በዓይን ሞራ ግርዶሽ ከ600 ሺህ  በላይ የሚሆኑ ዜጎች በሽታው እንዳጋጠማቸው ይታወቃል'' ያሉት ጀኔራል ዳይሬክተሩ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ልዩ ስትራቲጂክ እቅድ ወጥቶ  ክልሎችና የሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የትራኮማ ተጠቂዎችም በብዛት እንዳሉ ገልጸው፤ ችግሮቹን ከሚያባብሱት ነገሮች መካከል በዘርፉ የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል አለመኖሩ በመሆኑ የሰው ሃይል ለማልማት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ''በኢትዮጵያ 10 የዓይን ስፒሻሊስት ሃኪሞች ብቻ ይገኛሉ'' ያሉት ዶክተር ዳንኤል ሃኪሞቹ የሚገኙት በከተሞች ላይ በመሆኑና አገልግሎቱን በብዛት የሚፈልጉት ገጠር ላይ የሚገኙት የህብረተሱ ክፍሎች በመሆናቸው ችግሩን ማባባሱን ገልጸዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የዓይን በሽታ ትኩረት የሚሻ መሆኑን  በመገንዘብ  ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውስጥ በማካተት እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል እየተሰራበት መሆኑንም ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ለምለም አየለ በበኩላቸው ከ12 ዓመታት በፊት የተካሄደ ጥናትን አስታውሰው በወቅቱ በኢትዮጵያ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች የዓይን ብሌን ጠባሳ ችግር ተጠቂ መሆናቸው መታወቁን ገልጸዋል። ከችግሩ ስፋት አንጻር ሰፊ የሆነ ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና የዓይን ብሌን ለጋሾችን በማበራከት ችግሩን ለመቀነስ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የዓይን ባንኩ ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር እየሰራ ሲሆን አሁን ባለው የዓይን ብሌን ንቅለተከላ ፍላጎት አንጻር በቂ የሆነ የአገልግሎት ሽፋን አለመኖሩን ገልጸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም