በምእራብ ሀረርጌ ዞን የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ አፈፃፀም አነስተኛ ነው ተባለ

102
ጭሮ ግንቦት 12/2010 በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ወሳኝ ኩነቶችን በማስመዝገብ ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን የዞኑ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን ፀጋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በዞኑ ከ30 ሺህ በላይ ሰው ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን የተመዘገበው ከ12 ሺህ አይበልጥም፡፡ በልደት፣ ጋብቻ፣ ፍችና ሞት ከተመዘገቡት ኩነቶች መካከልም 7 ሺህ 744 ለሚሆኑት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። የህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረትና በየደረጃው ያለው አመራር ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት ጋር ተያይዞ ስራው በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን አብራርተዋል። በተለይ ከታች ያለውን ህብረተሰብ ለመድረስ ምዝገባው በብዛት በሚካሄድባቸው በቀበሌዎች ጽህፈት ቤቶች ቋሚ ሰራተኛ አለመኖር ስራውን እየሰሩ የሚገኙት የየቀበሌው ስራ አስኪያጆች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህ ደግሞ የቀበሌው ስራ አስኪያጆች ስራውን እንደተጨማሪ ስራ ስለሚያዩት በስራው የተሻለ አፈፃፀም ማሳየት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ የእቅዱን ግብ ለማሳካት በአሁኑ ወቅት የአፈፃፀም ድክመት ያለባቸውን ወረዳዎች በመለየት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ የግንዛቤ ክፍተቱን ለመሙላት ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኦዳቡልቱም ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ  መሃመድ ጁኔዲ በበኩላቸው ''በየደረጃው ባለው መዋቅር የሰው ሀይል አለመሟላት፣ የግንዛቤ ክፍተትና ሌሎችም ችግሮች ስራውን በሚፈለገው ልክ እንዳንሰራ አድርጎናል'' ብለዋል፡፡ በኦዳቡልቱም ወረዳ የቦሶሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰለሞን አበበ ''በወሳኝ ኩነት መመዝገብ ያለው ጠቀሜታ ግንዛቤ አልነበረኝም'' ብለዋል፡፡ አሁን ግን ግንዛቤ በማግኘታቸው ካሏቸው ሶስት ልጆች ሁለቱን በልደትና አንዱን በጋብቻ ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። የወሳኝ ኩነት ምዝገባ  ለአንድ አገር የመረጃ ምንጭ መሆኑን  በልማት ቡድናቸው በሚያካሂዱት ውይይት ትምህርት ማግኘታቸውን  የተናገሩት ደግሞ የዚው ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሄለን አሰግድ ናቸው፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም ልጃቸውን በማስመዝገብ የልደት ሰርቲፊኬት መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ዓመት በተደረገ ጥረት ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማካሄዳቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም