ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ የጥራት ችግር ይስተዋላል

83
አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ አሁንም የጥራት ችግር እየተስተዋለ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ። ይሁንና እነዚህን የጥራት ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው። በሚኒስቴሩ የዕጽዋት ጤናና ምርት አጠባበቅ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልደሃዋርያት አሰፋ እንደተናገሩት፤ ወደ ውጭ በሚላኩ በግብርና ምርቶች ላይ የጥራት ችግሮች ይስተዋላል። በችግሮቹም ከአምራቹ አንስቶ መጨረሻው የምርት ተቀባይ ወይም ሸማች እስኪደርስ ድረስ ባሉት የእሴት ሰንሰለቶች ችግሮቹ በተለያዩ መጠኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህም ደግሞ ሁሉም የእሴት ሰንሰለቱ ተዋናዮች የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል በቂ ግንዛቤና ክህሎት ማጣት ለችግሩ መስፋፋት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው የተናገሩት። ለአብነትም በቅርቡ ወደ አውሮፓ በሚላከው የበርበሬ ምርት ላይ ክብደት እንዲያነሳ በላኪዎች ውሃ ተጨምሮበት በአፍላ ቶክሲን እንዲጠቃ መደረጉን አንስተዋል። በተመሳሳይ ወደ አውሮፓና ህንድ በሚላኩ ቅመማ ቅመሞች ላይ የአፍላቶክሲን ችግር እንዲሁም በጥራ ጥሬዎች ላይም ደግሞ የጸረ-ተባይ ቅሪት እያጋጠመ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም አምራቹና ነጋዴው ለሌሎች በሽታዎች የሚረጩ መድኃኒቶችን በስህተት በመጠቀም የመነጨ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ካለመኖር የሚመነጭ መሆኑን ገልጸው ይህም ገበያውን በአሉታዊ መልኩ እንደሚጎዳው ነው ያረጋገጡት። ጎን ለጎንም ጥራትን ሊያስጠብቁ የሚችሉ መሰረተ-ልማቶች ማለትም ቤተ-ሙከራን ጨምሮ የቴክኖሎጂ ግብዓት እጥረት መኖሩን ገልጸዋል። በዘርፉ ያለው የአሰራር ሥርዓት ክፍተትና የቅንጅት አሰራር አለመዳበርም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፈተና ሆኖብናል ብለዋል። በዚህም መሰረት ወደ ውጭ የሚላኩት ምርቶቹ የተቀባይ አገራት መስፈርት ባለማሟላታቸው ምርቶቹ የሚመለሱበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰዋል። ሚኒስቴሩም ይህን ከግምት በማስገባት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት አጠናክሮ መቀጠሉን ነው አቶ ወልደሃዋርያት የተናገሩት። በቤተ-ሙከራም ጭምር ጥራቶችን የማረጋገጥ ሥራው ክፍተቶች ቢኖሩም ሚኒስቴሩ ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ለማከናወን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከርም የምርቶችን ጥራት ለማሟላት እንደሚሰራ አስረድተዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም