የኢትዮ-ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ሠራተኞች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ አበረከቱ

64
ነቀምቴ መስከረም 25/2011 የኢትዮ-ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ሠራተኞች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 200 ሺህ ብር ግምት ያለው የእለት ደራሽ እርዳታ አበረከቱ ። የሪጅኑ ሰራተኞች ድጋፍ ያደረጉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን የኢንዳይሬክት ቻናል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ገመቺስ ታደሰ እንደገለፁት የድርጅቱ ሠራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ተፈናቃዮቹ ጎብኝተዋል፡፡ ሰራተኞቹ በመጠለያ ጣቢያዎች ተገኝተው ተፈናቃዮችን ከተመለከቱ በኋላ ለችግሩ ሰለባ ለሆኑ  ህፃናት ቅድሚያ በመስጠት ለተፈናቃዮቹ  የገዙትን አልሚ ምግብና ሳሙና ለግሰዋል፡፡ ከኢትዮ-ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ሠራተኞች መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉዓለም ኃይለማሪያም በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊትም የሪጅኑ ሠራተኞች ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖችም 710 ሺህ ብር ከደመወዛቸው ቀንሰው መርዳታቸውን አስታውሰዋል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ እንደ አንድ የሪጅኑ ሰራተኛ የሚጠበቅባቸውን ድጋፉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ወይዘሮ ሙሉ አለም  ተናግረዋል፡፡                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም