በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ስር የተቋቋሙ የተማሪዎች ህብረት አደረጃጀቶች በጋራ የሚተዳደሩበት ደንብ ተዘጋጀ

243
ጎንደር ግንቦት 12/2010 በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ስር የተቋቋሙ የተማሪዎች ህብረት አደረጃጀቶች በትምህርት ጥራትና በሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት በጋራ የሚተዳደሩበት ደንብ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ህብረት አስታወቀ፡፡ 33ኛው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ህብረት መደበኛ ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትናንት ተጀምሯል፡፡ በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ አህመድ ሙክታር እንደተናገረው የጋራ ደንቡ መዘጋጀት የህብረቱን ተናጠላዊ እንቅስቃሴ በጋራ ለማስተባበር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ''በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ስር የተቋቋሙ የተማሪዎች ህብረት አደረጃጀቶች በትምህርት ጥራት፣ በሰላማዊ የመማር ማስተማርና በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራና በቅንጅት እንዲሰሩ መተዳደሪያ ደንቡ ያግዛል'' ብሏል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ የዩኒቨርሲቲዎቹ የተማሪዎች ህብረት በጋራ ተቀራርበው በመስራት አንዱ ከሌላው ልምድ የሚቀስሙበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የተማሪዎችን ተሳትፎና አንድነት የማጠናከር ተልእኮ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ በ33ኛው የህብረቱ ጉባኤ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ከጸደቀ በኋላም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ስር የሚገኙ የተማሪዎች ህብረት አደረጃጀቶች ተግባራዊ የሚያደርጉት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ መንገሻ አበራ በበኩሉ አዲሱ የህብረቱ መተዳደሪያ ደንብ የዩኒቨርሲቲዎችን ትስስር በማጠናከር መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የትንሸዋ ኢትዮጵያ ማሳያ እንደመሆናቸው ህብረቱ የተማሪዎችን ድምጽ ወክሎ መብታቸው እንዲከበርና ግዴታቸውንም እንዲወጡ ከዩኒቨርሲቲዎች አመራሮችና ከተማሪዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የኦዳቡልቱ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት የሴቶች ጉዳይ ተጠሪ ተማሪ እየሩሳሌም አለሙ ''የህብረቱ ጉባኤ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ ነው'' ብላለች፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ የተማሪዎች ህብረት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን በማድረግ በኩል ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ አካላት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ''ህብረቱ በተማሪዎች መካከል የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአንድነት እሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና ነበረው'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወደፊትም ይህንኑ ተልእኮውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ በጉባኤው በታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በዜጎች ሰብኣዊ መብት አከባበርና የህይወት ክህሎት አመራር በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ በተጋባዢ        እንግዶች ገለጻና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ የህብረቱ ጉባኤ በሁለት ቀናት ቆይታው ባለፉት 9 ወራት ያከናወናቸው ተግባራት በሪፖርት ቀርቦ የጋራ ውይይት ያካሂዳል፡፡ በጉባኤው በሀገሪቱ ከሚገኙ 44 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዘዳንቶችና ስራ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺ በላይ አባላትን አቅፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም