ኢህአዴግ በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ውሳኔዎች ያስተላልፋል ብለን እንጠብቃለን -ምሁራን

71
ነቀምቴ መስከረም 25/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ)ድርጅታዊ ጉባዔ ውስጣዊ ችግሮቹንና ጉድለቶቹን የሚያስወግድባቸውንና የአገሪቱ ዕጣ ፈንታን በሚወስኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች ያስተላልፋል ብለው እንደሚጠብቁ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። ምሁራኑ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ኢህአዴግ በሐዋሳ እያካሄደ ባለው 11ኛው ድርጅታዊ  ጉባዔ ያሉበትን ችግሮችና ጉድለቶች በሚፈታባቸውና በአገሪቱ መጻኢ ዕድል ላይ ይወስናል የሚል እምነት አላቸው። የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ደምስ ፍርዲሳ ድርጅቱ ውስጣዊ  ችግሮቹን በዝርዝር በመፈተሽ የአገሪቱን የወደፊት አቅጣጫዎች የሚወስኑ መፍትሄዎችና ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። በጉባዔው በአንዳንድ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች የሚወገዱበት አቅጣጫ ይቀመጣል ብለውም ይጠብቃሉ። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የሚታዩ የሃሳብ ግጭቶች ተለይተው በምክክር የሚፈቱበት መድረክ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ዶክተር ደምስ ገልጸዋል ። ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ የመወዳደሪያ መድረክ በመፍጠር እየታየ ያለውን የአንድነት፣የዴሞክራሲና የፍቅር ጭላንጭል ተጠናክሮ  እንዲቀጥል የሚረዱ ጠቃሚ ውሳኔዎች እንጠብቃለን ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። በዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር ድሪባ ደምሰው በበኩላቸው ጉባዔው በአገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች እየታዩ ያሉትን የሰላምና መረጋጋት እጦት ችግሮች የሚገቱበትና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት አቅጣጫ ያስቀምጣል ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል። ውሳኔዎቹ በአገሪቱ የተጀመረውን የአንድነትና የፍቅር እንቅስቃሴ በቀጣይነትና በዘላቂነት ለማስቀጠል ሚና ይጫወታሉ ሲሉም ተናግረዋል። የአገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ፍትሃዊ የሀብት  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ትኩረት ይሰጣል ብለው ይገምታሉ። በዩኒቨርሲቲው የቋንቋ መምህር ተፈሪ ተረፈ በበኩላቸው ጉባዔው አገሪቱን ወደፊት የሚያራመድ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው አመራሮች ያሉበት እንደመሆኑ መጠን፤አገሪቷንና ሕዝቦቿን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ድርጅታዊ ጉባዔውን ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም