በጉጂ ዞን የተከሰተውን የዋግ በሽታ ለመከላከል የመድኃኒት እጥረት እንደገጠማቸው አርሶ አደሮች ገለጹ

72
ነገሌ መስከረም 25/2011 በጉጂ ዞን በቦሬና አናሶራ ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የዋግ በሽታ ለመከላከል የመድኃኒት እጥረት እንደገጠማቸው አርሶ አደሮች ገለጹ። የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት እጥረቱን ለመፍታት እየጣርኩ ነው ይላል። የወረዳዎቹ አርሶ አርሶአደሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  እንዳመለከቱት በሽታውን የሚከላከሉበት መድኃኒት ስላልቀረበላቸው ሰብላቸው ላይ ጉዳት እየደረሰበት ነው። መንግሥት መድኃኒቱን በማቅረብ ሰብሉን ከአደጋ እንዲታደገውም ጠይቀዋል። በአናሶራ ወረዳ የይርባ ቡልዩ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጩሉቄ ኡዶ በሰጡት አስተያየት በሽታው በተለይ የባቄላ ፣ የገብስና ስንዴ ሰብሎችን እያጠቃባቸው ነው ።በተለይ ባለፉት 15 ቀናት በሰብላቸው ላይ የተከሰተውን በሽታ ለመከላከል  ያደረጉት ጥረት በመድኃኒት እጥረት ሊሳካ አልቻለም። በሽታው  በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የዘሩትን ባቄላ ቅጠሉን እያደረቀው ሲሆን፣ በአንድ ሄክታር ተኩል የዘሩት ስንዴ ደግሞ ቅጠሉ ቢጫ መልክ መሆን ጀምሯል ብለዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ የራያ ቦዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መኤሳ ገመዳ በበኩላቸው መንግሥት በነፃ ሲያቀርብላቸው የነበረውን መድኃኒት ከአዶላ ከተማ በሊትር 450 ብር በመግዛት  በሽታውን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። በሽታው ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋ መምጣቱን የሚገልጹት አርሶ አደሩ፣በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል መንግሥት መድኃኒቱ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡ በዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አንተነህ ፈዬራ በወረዳዎቹ ለበሽታው ከተጋለጠው 667 ሄክታር መሬት  የበሽታው ስርጭት ጎልቶ በታየባቸው አካባቢዎች 150 ሊትር መድኃኒት በመርጨት ቡቃያውን ከበሽታው መጠበቅ ተችሏል ብለዋል ። ለዞኑ የቀረበው መድኃኒት በቂ ባለመሆኑ ከአሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተጠየቀው 300 ሊትር መድኃኒት ወደ ዞኑ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ከጉጂ ዞን በ2010/11 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 115 ሺህ ሄክታር መሬት ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም