ለአደጋ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሁሉም አካላትን የተቀናጀ ድጋፍና ትብብር ይጠይቃል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

366

ድሬደዋ(ኢዜአ) የካቲት 2/2015 ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ሲል የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የፌደራልና የክልሎች የአደጋ ስጋት ቅነሳ ኮሚሽኖች የ2015 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ የተሰሩ ተግባራትን በመገመገም ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የተጀመረው የተናበበ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ለአደጋ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ተግባራት ላይ የተቀናጀ ጥረቱ መጠናከር አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም በ2030 ዓ.ም ለአደጋዎች የማይበገር አገርና ማህበረሰብ ለመገንባት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ለአደጋ ለተጋለጡ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።

የአደጋ ስጋት ዘላቂ መፍትሄ እንደ አገር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮችን ተቀናጅቶ ዳር ማድረስ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም የሁሉንም አካላት ርብርብ ይፈልጋል ብለዋል።

በግምገማው ላይ የተገኙት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የተጀመረው ርብርብ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በተለይም የአደጋ ስጋትን መቀነስና አደጋው እንዳያጋጥም መከላከል የሁሉም ተቋማትና በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በልማትና ዕድገት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረው ይህንን ችግር በጊዜያዊና በዘላቂነት ለመቀነስና ለመከላከል የወጡ አሠራሮችንም በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ነው የገለፁት።

በምክክር መድረኩ ላይ የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገኦ እና አባላቱ፤ የሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አመራሮች እና የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ መድረክ ከስራ አፈጻጸም ግምገማው በተጨማሪ የአእምሮ ማጎልበቻ ስልጠናዎች እንደሚሰጡና የተለያዩ የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ረቂቅ የህግ ማዕቀፎች ላይም ውይይት እንደሚደረግ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም