በገንዳ ውሃ ከተማ በ92 ሚሊዮን ብር ወጪ የመሰረተ ልማት ስራ እየተከናወነ ነው

184

መተማ፣ የካቲት 02/2015(ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር በ92 ሚሊዮን ብር ወጪ የህዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልሱ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን የአስተዳደሩ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ገበያው መንግስቴ ለኢዜአ እንደተናገሩት የከተማዋን መሰረተ ልማት በማሻሻል ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

የመሰረተ ልማት ስራዎቹ ግንባታ እየተካሄደ ያለውም ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከዓለም ባንክና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመሰረተ ልማቶቹ መካከል የትምህርት ቤት ማስፋፊያ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ፣ የወጣት ማዕከል፣ የጠጠር መንገድና ሌሎችም እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የመሠረተ ልማት ስራዎቹን ጥራት ለማስጠበቅም ከዲዛይን ስራ ጀምሮ በግንባታ ሂደቱ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ግንባታዎቹንም በመጪው ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታው ለ3 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩንም ጨምረው ገልፀዋል።

ህብረተሰቡ የሚገነቡትን መሰረተ ልማቶች ጥራት ከመከታተል ባለፈ ገንዘብ በማዋጣት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም አስረድተዋል።

በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው በተለምዶ አየር ማረፊያ ተብሎ የሚጠራው መንገድ የድንጋይ ንጣፍ ስራ እየተሰራ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

በከተማዋ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች የከተማዋን ገፅታ የሚቀይሩና እድገቷን የሚያፋጥኑ በመሆናቸው በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲከናወን ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች የህዝቡን የልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈም ለስራ እድል ፈጠራ ጠቅሞናል ያለው ደግሞ 22 ሆነው በመደራጀት በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ የተሰማራው ወጣት መለሰ ሀብታሙ ነው።

ባለፈው ዓመት እያንዳንዳቸው ከ60 ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኙ መሆናቸውን ተናግሮ፤ በዚህ ዓመትም ካለፈው ዓመት የተሻለ ገቢ እናገኛለን የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጿል።

በዚህ ዓመት የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች የከተማዋን የመሰረተ ልማት ሽፋን ወደ 55 በመቶ ማሳደግ እንደሚያስችሉም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም