ለ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች

357

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 ለ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች።

ለ36ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔና ለ42ኛው የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የጉባዔው ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ አባላት ጎብኝተዋል። 

የጉባኤው ተሳታፊ መሪዎችና ሌሎችም እንግዶች በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ የመዲናዋ ገጽታ ይበልጥ ማራኪ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ፤ ለጉባዔው ስኬታማነት ከሁለት ወራት በፊት ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። 

በአዲስ አበባ በሁሉም መልኩ እንግዶችን በሚያምርና በጥሩ መስተንግዶ ለመቀበል የተደረገው ዝግጅትም አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል። 

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና የሌሎች አገራት ተወካዮችም በጉባዔው የሚሳተፉ መሆኑን ጠቁመው፤ እንግዶችን ለመቀበልም ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጀማሉ ጀምበሩ፤ የአፍሪካ መናገሻ የሆነችው አዲስ አበባ እንግዶቿን ለመቀበል አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አጠናቃለች ብለዋል። 

36ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ "የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ማፋጠን" በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል። 

ከመሪዎቹ ጉባዔ ቀደም ብሎም የካቲት 8 እና 9 የውጭ ጉዳይ የሚኒስትሮች ስብሰባ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም