የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእንግሊዝ የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት እድሎች እና አማራጮች ላይ ማብራሪያ ሰጠ

238

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእንግሊዝ የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት እድሎች እና አማራጮች ላይ ዛሬ ማብሪሪያ ሰጥቷል።

ለልዑኩ ገለጻ ያደረጉት በሚኒስቴሩ የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ናቸው

አምባሳደር እሸቴ ከእንግሊዙ የፋይናንስ ኩባንያ ‘Jeffries International Limited’ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እና የእቅድ ባለሙያ ታቶ ሞሳድል ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስኩ ስላሉ የማበረታቻ ማዕቀፎች እና እድሎች እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ኩባንያዎች በአገሪቷ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተም አምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ልዑካን ቡድኑ ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጎ በመምረጡ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

መንግስት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተቀመጡ ጉዳዮችን ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑም አምባሳደር እሸቴ ለልዑካን ቡድኑ ገልጸውላቸዋል።

በተጨማሪም በብሔራዊ ምክክር አማካኝነት በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የሚያስችሉ ስርዓቶች በማስቀመጥ ላይ እንደሚገኝ አምባሳደሩ ገለጻ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።

የእንግሊዝ የንግድ ልዑካን ቡድን መሪ ታቶ ሞሳድል በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ እየተተገበረበት ያለውን ፍጥነት እና የኢትዮጵያ መንግስት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጎልበት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችን ማድነቃቸውን ጠቁሟል የሚኒስቴሩ  መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም