የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ የመጀመሪያው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው

268

ድሬዳዋ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ የመጀመሪያው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚዘልቀው የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ የመጀመሪያ ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በአምስት የወንዶች እና በአራት የሴቶች ክለቦች መካከል ከትናንት ጀምሮ በድሬዳዋ እየተካሄደ ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከድሬዳዋ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ውድድር እስከ የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቀጥል ታውቋል። 

ውድድሩ በምስራቅ አፍሪካ ብቁና ተፎካካሪ ክለቦችን እንዲሁም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል። 

በውድድሩ በወንዶች ምድብ ሃዋሳ፣ ሰበታ፣ ወልቂጤ፣ ፋሲል እና ድሬዳዋ ከነማ ክለቦች እንዲሁም በሴቶች ምድብ ደግሞ ወልቂጤ፣ ሃዋሳ፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተሳተፉ ይገኛሉ። 

ትላንት በወንዶች ምድብ በተከናወኑ የመክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ድሬዳዋን 55 ለ45፤ ሰበታ ደግሞ ሃዋሳን 65 ለ61 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። 

ዛሬ በተከናወኑ የሴቶች ምድብ ጨዋታዎች ወልቂጤ-አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 44 ለ32፤ ሃዋሳ ባህር ዳር ከነማን 68 ለ34 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። 

በወንዶች ምድብ ዛሬ በተከናወኑ ውድድሮችም ሃዋሳ ፋሲልን 67 ለ31፤ ሰበታ ወልቂጤን 52 ለ48 ማሸነፍ ችለዋል። 

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት አሳምነው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በየዓመቱ ውድድሩ የሚካሄደው የቅርጫት ኳስ ህዝባዊ መሠረቱን በማጠናከር ህብረተሰቡ በየደረጃው ከስፖርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ነው። 

"በተለይ በዘርፉ ተተኪና ምርጥ ስፖርተኞችን በማፍራት የአገራችንን ተፎካካሪነት ለማሳደግ ያግዛል" ያሉት አቶ ዳዊት፣ "የውድድሩ አሸናፊ ክለቦች በምስራቅ አፍሪካ የቅርጫት ኳስ የሻምፒዮና ውድድር ላይ ይካፈላሉ" ብለዋል። 

ዓመታዊ ውድድሩ በአገሪቱ አምስት የተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄድና በድሬዳዋ እየተካሄደ ያለው የፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ የመክፈቻ ወድድር መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም