በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ ይሻሉ- የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ

266

አዲስ አበባ የካቲት 1/2015(ኢዜአ) ፦በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልግ መሆኑን የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ገለጸ።

በክልሉ መንግሥትና በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ትብብር ለችግር ለተዳረጉ 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ወገኖች እስከ አሁን ድጋፍ መደረጉም ታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ ሁለቱ ጉጂዎች፣ የምስራቅ ሐረርጌ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በባሌ ቆላማ አካባቢ በአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ሳይዘንብ ቀርቷል።

በዚህም ምክንያት በክልሉ በአሥር ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 152 ወረዳዎች ድርቅ ተከስቶ በተለይም በእንስሳት ኃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ለችግር ተዳርገዋል።

የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በድርቁ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከክልሉ መንግሥት እና የአደጋ ስጋት አመራር ጋር በመሆን ለችግር ለተዳረጉ 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም እስከ አሁን 12 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ግምት ያለው 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የእርዳታ እህል ተደራሽ የተደረገ ሲሆን ውሃ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎችም በተሽከርካሪ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል።

በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በሁለቱ ጉጂዎች የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በወለጋ በጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ዜጎችም 90 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ተደራሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቦረና ዞን በ13 ወረዳዎች ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውሰው፤ በእንስሳትም ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል የመኖ አቅርቦት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የድርቁ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ቁጥር ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ወደ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከፍ በማለቱ የድጋፍ ሁኔታው መጠናከር አለበት ብለዋል።

በአደጋዎቹ ሳቢያ ጉዳት ላይ ለሚገኙ ዜጎች መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ቢሆንም ከእርዳታ ፈላጊው አንፃር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በድርቁ ምክንያት ከመስከረም ወር ጀምሮ እስከ አሁን በቦረና ዞን ብቻ ከ47 ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሞቱት የቀንድ ከብቶች ከ100 ሺህ በላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ በድርቅና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ የሚሹ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ኮሚሽን በመባል ይታወቅ የነበረው የክልሉን ሕዝብ ነባር የመረዳዳት እሴት መሰረት አድርጎ የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ በሚል ባለፈው ዓመት መቋቋሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም