በጋሞ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 884 የክስ መዝገቦች በእርቅ መፈታታቸው ተገለጸ

192

አርባ ምንጭ፣ የካቲት 01 ቀን 2015 (ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 884 የፍታሐብሔር እና የወንጀል ክስ መዝገቦች በእርቅ መፈታታቸዉን የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የክስ መዝገቦቹ በእርቅ መፈታታቸዉ የህዝቡን ማህበራዊ ግንኙነትና አንድነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንዷለም አምባዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከቀረቡ 12 ሺህ 745 የፍታሃብሔርና የወንጀል ክስ መዝገቦች ውስጥ 9 ሺህ 802 መዝገቦች ዉሳኔ አግኝተዋል።

ፍርድ ቤቱ የደንበኞችን ፍትህ የማግኘት መብት ለማስከበር የተለያየ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተለይም ፍርድ ቤቱ ክሶችን በባህላዊ የፍርድ ሂደት እንዲፈቱና ዘላቂ እርቅ እንዲፈጠር እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በግማሽ ዓመቱ 369 የፍታሐብሄር እና 515 በአጠቃላይ 884 የክስ መዝገቦች በእርቅ እንዲፈቱ መደረጉን ገልጸዋል።

የክስ መዝገቦችን በእርቅ እንዲፈቱ የማድረግ ተሞክሮ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፤ ፍርድ ቤቱ ክሶች በእርቅ እንዲፈቱ የማድረግ ሂደትን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል ፡፡

በአከባቢው ማህበረሰብ ዕሴት መሰረት በእርቅ የሚጠናቀቁ የፍትህ ሂደቶች ባህልን ከማክበር ከዕምነትና ህሌናዊ ፍርድ የሚያያዙ በመሆናቸው ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን አቶ አንዷለም ገልጸዋል።

የክስ መዝገቦች በእርቅ እንዲፈቱ የጋሞ ዞን ህዝብ ቱባ የባህል ስርዓት ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዉ፤ ይህም የፍርድ ቤቱን ጫና ከመቀነስም በላይ የህዝቡን ማህበራዊ ግንኙነትና አንድነት እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የጋሞ ባህል በመሠረቱ ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለአንድነት ትልቅ ስፍራ እንዳለው የገለጹት የጋሞ ዞን ሀገር ሽማግሌ አቶ አመሌ አልቶ፤ በእርቅ ችግሮችን መፍታት በዘላቂነት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የክስ መዝገቦችን አጣርቶ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ በማስረጃ ለማረጋገጥ የሚገደድ መሆኑን የጠቀሱት የሀገር ሽማግሌው፤ በባህላዊ የእርቅ ስርዓት መዋሸት “ጎሜ” ወይም ቅስፈት በመሆኑ እውነቱን ማውጣት እንደሚቻል ተናግረዋል።

እውነቱን በመጨበጥ ሽማግሌዎች ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ብይን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍርድ ስርዓቱን ከህዝቡ ባህላዊ መሰረት ጋር በማስተሳሰር ችግሮች በእርቅ እንዲፈቱ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጠቆሙት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ አቶ ጩባ ጭኖ ናቸዉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም