የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የስብራቶች ሁሉ መፍቻ በመሆኑ ጥራትን የማስጠበቅ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው-ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሠ ጃለታ

298

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 01/2015 በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የስብራቶች ሁሉ ችግር መፍቻ በመሆኑ ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ባህል ጥናት ተመራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሠ ጃለታ ገለጹ።

የትምህርትና ባህል ጥናት ተመራማሪና መምህሩ ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሰ ጃለታ፤ በትምህርት ስርአት፣ ጥራትና ተደራሽነት ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።  

የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ብቃትና ጥሩ ሰብዕና ያለው ዜጋ እንዲያፈራ በማድረግ በሁሉም መስክ የነበሩ ስብራቶችን ማስተካከል ይቻላል ብለዋል።

የፖለቲካ ስርዓቱን ስብራት ለማስተካከል በዋነኝነት በምክንያት የሚያምን ትውልድ መፍጠር ይገባል ያሉት ተመራማሪው ለዚህም የትምህርት ስርዓቱ መስተካከልና የጥራት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ስርዓቱ በምክንያት የሚያምን ዜጋ መፍጠር ከቻለ የህዝብን አንድነት እና የህዝብን ጥቅም የሚያሥቀድም የፖለቲካ ስርዓትን መገንባት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡  

የትምህርት ስርዓቱ በትክክለኛው መንገድ ከቀጠለና ጥራትን ማስጠበቅ ከተቻለ ከፖለቲካ ስብራቱ ባለፈ እየተንከባለሉ የመጡ የተለያዩ አገራዊ ችግሮችን ማስተካከል ይቻላል ብለዋል።

የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ለሁሉም ችግሮች "መፍቻ ቁልፍ ነው" ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስብራት ችግሮች እንድሁም የሰላም እጦት ችግሮች በሂደት ይፈታሉ ሲሉ ገልጸዋል።  

የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ጉዳይ የትህምርት ተቋማት ሀላፊነት ብቻ ባለመሆኑ አጠቃላይ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተሳትፎና ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። 

በትምህርትና በቴክኖሎጂ እውቀት የበቃ ዜጋ ማፍራት ከተቻለ የችግሮች ሁሉ መፍትሄ ቀላል ይሆናልም ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም