ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ ሰብል እና የእንስሳት ልማት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንሰራለን--የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት

186

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 1/2015 ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ ሰብል እና የእንስሳት ልማት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደሚሰራ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሞድዚ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት (ፋኦ) የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው ድጋፍ የሚፈልጉ እና ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሞድዚ በበኩላቸው የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ በአሁኑ ወቅት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየሰራ ያለውን ስራዎች ተቋማቸው አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ተወካይዋ አክለውም በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ ሰብል እና የእንስሳት ልማት ላይ ተቋማቸው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስቴር በዘርፉ በቁርጠኝነት ለመስራት መስማማታቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም