የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በሚሲዮኖች የተጠናከረ የማስተዋወቅ ተግባር በትኩረት ይሰራል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

225

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በሚሲዮኖች የተጠናከረ የማስተዋወቅ ተግባር በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የመንግስት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ሰራተኞች በባለሃብቱ የሚነሱ ቅሬታዎችን በፍጥነት መፍታት የሚያስችል የአሰራር ስርአትን መዘርጋት አለባቸው ብለዋል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ የፖሊሲ ምክክር ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ መዋለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ የውጭ ባለሀብቶች ችግሮች በሚገባው መጠን መፍታት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል።

ለዚህም በሁሉም እርከኖች ያሉ የመንግስት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ሰራተኞች በባለሃብቱ የሚነሱ ቅሬታዎችን በፍጥነት መፍታት የሚያስችል የአሰራር ስርአትን መዘርጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በአገር ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ውጭ ባሉ ሚሲዮኖች የተጠናከረ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የፖሊሲ ምክክሩ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና በወሎ ዩኒቨርስቲ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተካሄደባቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተደድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም