በደብረ ብርሀን ከተማ ከ359 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

209

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ጥር 30/2015 የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከ359 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ባየ እንደገለጹት፣ የከተማዋን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በእዚህም ከክልሉ መንግስት፣ ከዓለም ባንክ እና ከከተማ አስተዳደሩ በተገኘ በ359 ሚሊዮን ብር ወጪ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ 35 የልማት ፕሮጀክቶችን እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል ባለ ሰባት ወለል የከተማ አስተዳደር ሕንፃ ግንባታ፣ የአጼ ምኒሊክ ፓርክ፣ ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ዲፖ፣ የአራት ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታና ሌሎች ግንባታዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት የሚከናወኑት የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ትኩረት በመሰጠቱ እስካሁን ድረስ አራት የልማት ፕሮጀከቶች መጠናቀቃቸውንና የሦስቱ አፈጻጸምም 95 በመቶ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ቀሪ የልማት ፕሮጀክቶች በተለያየ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ነብዩ፣ ለአስፓልት መንገድ ሥራዎች ጨረታ ወጥቶ ስራውን ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ፣ በዚህ ዓመት በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ለ1ሺህ 500 ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል።

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ቀለሟ ሀብቴ በበኩላቸው ከአንድ ዓመት ወዲህ በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ተገንብተው እየጠናቀቁ ስለመሆኑ መታዘባቸውን ገልጸዋል።

"ይህም የከተማዋን የእድገት ደረጃ ከፍ ከማድረግ ባለፈ ነዋሪዎቹን የልማት ተጠቃሚ እያደረገን ነው" ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበርካታ ኢንዱስትሪዎችና ኢንቨስትመንቶች መናኻሪያ እየሆነች በመምጣቷ ለመሰረተ ልማት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም