የፀማይ ህዝብ የዘመን መለወጫ ''ባርባይሳ'' በሲምፖዚየምና በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

253

ቀይ አፈር (ኢዜአ) ጥር 30/2015 የፀማይ ህዝብ የዘመን መለወጫ ''ባርባይሳ'' በሲምፖዚየም፣ ፓናል ውይይት እና በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በበና ፀማይ ወረዳ ቀይ አፈር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዳንኤል ዶብዮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የፀማይ ህዝብ በየአመቱ የካቲት 1 ቀን አሮጌውን አመት ሸኝቶ አዲሱን አመት ይቀበላል። 

በዚሁ መሰረት የዘንድሮ የአዲስ ዓመት መባቻና የአሮጌው ዓመት ማሰናበቻ በዓል በተለያዩ ክዋኔዎች በመከበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል። 

የ''ባርባይሳ'' በዓል ከጥንት አባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በርካታ እሴቶች ያሉት ክብረ በዓል ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ''ባርባይሳ'' በፄማኮ ቋንቋ የሁለት ቃላቶች ውህድ ሲሆን ''ባራ'' ማለት አዲስ አመት ''ባይሳ''ማለት ደግሞ መጀመሪያ የሚል ትርጉሜ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የ"ባርባይሳ" በዓል የፀማይ ባላባት የዘር እህል ባርኮ ሲሰጥ የበልግ እርሻ ዘር የሚዘራበት ሲሆን አካባቢው ሰላም እንዲሆን፣ ቂምና ቁርሾ እንዲወገድና ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ምርቃት የሚወሰድበት ነው ብለዋል። 

እንዲሁም ክፉ መንፈስ እንዲርቅ፣ በሽታ እንዲጠፋ፣ ጎተራው እንዲሞላ እና ከብቶች ጋጣ እንዲሞሉ በመሪ የሚመረቅበትና ወደ ፈጣሪ ተማፅኖ የሚደረግበት እለት እንደሆነ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል። 

በዓሉ ያለውን በመሸኘትና ትምህርት በመውሰድ ለቀጣይ ልማት፣ ተስፋ፣ ሰላምና አንድነትን እንዲሁም አብሮነትን ለመገንባት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል። 

ባህሉን በማጎልበት ለትውልድ ለማስተላለፍ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ በዓሉ በተለያዩ መርሃ ግብሮች መከበር መቻሉ የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል። 

የበዓሉን አጠቃላይ ይዘት ሰንዶ ከማስቀመጥ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል። 

በቀይ አፈር ከተማ በሲምፖዚየም፣ ፓናል ውይይትና በተለያዩ ባህላዊ ስርአቶች በድምቀት እየተከበረ በሚገኘው በዚሁ በዓል የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የባህል ተመራማሪዎች፣ የባህል መሪዎች እና የብሔረሰቡ አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

በነገው ዕለት ደግሞ የአዲስ አመቱ ብስራት በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች የፀማይ ባላባት መገኛ በሆነው በሉቃ ቀበሌ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ተመላክቷል። 

በክብረ በዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም