በስድስት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ884 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ተግባራት ተከናውነዋል

275

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 በአዲስ አበባ በስድስት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ884 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የከተማ አስተዳደሩ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዓለም ላይ በተለያዩ አገሮች የተለመደ የማህበራዊ አገልግሎት መሆኑ ይታወቃል።

በኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ባህል ተወስዶ በተለይም ወጣቶች በተለያዩ መስኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ወጣቶች ገንዘብና ጉልበታቸውን ለሕብረተሰብ ጥቅም ማዋላቸው እየተለመደ መጥቷል።

በዚህም በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑትን በጎ ተግባራት አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሁናቸው ጌትነት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በመዲናዋ ወጣቶች፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ልምድ እያደረጉና በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሕብረተሰቡን የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር፣ ሕገ-ወጥ ተግባራትን መከላከል፣ አቅመ ደካሞችን ማገዝና የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ፣ የደም ልገሳና ሌሎችም አገልግሎቶች ላይ ተሳትፎ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በእነዚህና መሰል የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ2 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች መሳተፋቸውን ያስታወሱት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ በስድስት ወራት ብቻ ከ884 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት ሰጥተዋል ብለዋል።

የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከተለያዩ አካላት በተሰባሰበው ሃብትም ከ117 ሚሊየን 60 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የባለሃብቶች ተሳትፎ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ለተሻለ ሥራ ተሳትፎና ትብብራቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በአሰራር ማዕቀፍ ለመምራት የማኅበራዊ ኃላፊነት ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ እንዲጸድቅ ማድረግ ብቻ እንደሚቀር ተናግረዋል።

የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ በዚህ ዓመት ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልጸው የማህበራዊና ኢኮኖሚ ፋይዳውም የላቀ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም