የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ30 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰልጣኞችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል

488

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2015 የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 30 ሺህ 900 አዲስ ሰልጣኞችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን የመዲናዋ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በመዲናዋ የተሟላ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስጠት የሚችሉ 15 ኮሌጆች ሰልጣኞችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል።

እነዚህ ፖሊኮሌጆች ከ158 ሺህ በላይ የሙያ ሰልጣኞችን ማስተናገድ የሚችሉ ቢሆንም አሁን እየተቀበሉት ያለው ከግማሽ በታች መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የሰው ሃይልና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ታሳቢ በማድረግ የሰልጣኖችን ቅበላ ከፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም 30 ሺህ 900 ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉን የሚያዘምኑ ስትራቴጂዎችና አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኮሌጆቹ በአጫጭር ስልጠና እና በመደበኛ ፕሮግራም በማሰልጠን ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለማፍራት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልማት ቢሮ የተቋማት ልማት ዳይሬክተር አምባቸው ግርማይ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አመለካከት በመቀየር አሁን ላይ ለውጦች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች በገበያው ላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ በመምጣቱም ጭምር በርካታ ወጣቶች ወደ ዘርፉ ስልጠና እየመጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራትና በተለይም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም