የምንተዳደርበትን የክልል አደረጃጀት በድምጻችን ወስነናል -በደቡብ ኦሞ እናቶች

239

ጂንካ ጥር 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) የምንተዳደርበትን የክልል አደረጃጀት በድምጻችን ወስነናል ሲሉ በደቡብ ኦሞ ዞን በውብሐመር ምርጫ ጣቢያ እየተካሄደ ባለው ህዝበ ውሳኔ የተሳተፉ እናቶች ገለጹ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ዎባ አሪ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ወይዘሮ ታደለች በኃይሉ እና ወይዘሮ ብርቱካን ጌታሁን ከአራስ ቤት ወጥተው ዛሬ እየተካሄደ ባለው የክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ ድምፃቸውን ሰጥተዋል ።

እናቶቹ የአራስነት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ጨቅላ ልጆቸውን ታቅፈው በውብሐመር ምርጫ ጣቢያ በመገኘት በህዝበ ውሳኔው በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል ።

በዎባ አሪ ወረዳ የዲራመር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ታደለች በኃይሉ የሚተዳደሩበትን የክልል አደረጃጀት በሚወስኑበት ህዝበ ውሳኔ መብታቸውን ሳይጠቀሙ እንዳያመልጣቸው ሲሉ ከአራስ ቤት ወጥተው ድምጽ መስጠታቸውን ገልጸዋል ።

በድምጽ መስጫ ጣቢያው አራስ በመሆናቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በመስተናገዳቸውና የመወሰን ዕድላቸውን መጠቀም በመቻላቸው ደስታ እንደፈጠረባቸው ወይዘሮ ታደለች ተናግረዋል።

"የምተዳደርበትን የክልል አደረጃጀት ለመወሰን ድምጼ ዋጋ እንዳለው በማመኔ ከአራስነቴ ተነስቼ ድምጼን ሰጥቻለሁ" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ብርቱካን ጌታሁን ናቸው።

"አራስነቴ ሳይገድበኝ ልጄን ታቅፌ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመምጣት ድምጼን ሰጥቻለሁ " ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም