ኢትዮጵያ አዲስ አስተሳሰብና የአእምሮ ልሕቀቱ ያዳበረ ዜጋ ትፈልጋለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

82
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ አዲስ አስተሳሰብና የአእምሮ ልሕቀት ያዳበረ ዜጋ እንደሚያስፈልጋት አመላከቱ። በዶክተር ምሕረት ደበበ ዳሬክተርነት የሚመራው 'የማይንድ ሴት ኮንሰልት ኮንቬንሽን ዝግጅት' ትናንት በሚሌኒየም አዳራሽ የሀይማኖት አባቶች፤ የመንግስት ባለ ስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ተከናውኗል። በዝግጅቱ አዳዲስ አስተሳሰብ የሚያዳብሩ፣ አነቃቂ፣ ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያተኩሩ ሐሳቦች ተንጸባረቀዋል። የኮንቬንሽኑ ዳሬክተር ዶክተር ምሕረት ደበበ፤ 'ሐሳብ ሰው ካገኘ ክንፍና እግር ይኖረዋልና ትውልድን መቀየርና ልሕቀትን መገንባት ይቻላል' ብለዋል። የጋራ ሐሳብ በማዋጣት አገርን ለመገንባት፤ ትልቁን የአገሪቷን ሕዝቦች መጠን የሚይዘው ወጣት ጋር በመድረስ የአስተሳሳብ ልሕቀት ላይ መስራት ማስፈለጉንም ጠቁመዋል። በዝግጅቱ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደገለጹት፤ አዲስ ሐሳብ አሮጌውን ከአዲሱ አስማምቶ የተሻለውንና የሚመጣውን ካለፈው ጋር ለማጣጣምና አገርን ለማስቀጠል ሚናው ትልቅ ነው። "አንተ ስትታመም ኢትዮጵያ ትታመማለች፤ አንተ ስትታሰር ኢትዮጵያ ትታሰራለች፤ አንተ ስትማር ኢትዮጵያ ትማራለች" ያሉት ዶክተር አብይ አንዱ ሲከፋ እንደራሱ የሚመለከትና የሚተሳሰብ  ዜጋ ለመፍጠር አዲስ ሐሳብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 'አዲስ ሀሳብ የሰው ልጅ በዘመኑ ሁሉ ሲፈልገው፤ ሲደክምበት የነበረ ነገር ነው' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰው ልጅ ለውጥን ከመፍራትና ከመሸሽ ለውጥ አይቀሬ መሆኑን በማመን አሮጌውን አስተሳሰብ ከአዲሱ ጋር አስማምቶ መሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል። 'ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን የማለም፤ ነገን ማሰብ እንዲሁም አዲስ ሐሳብን በልበ ብርሃንነትና አስተዋይነት  ማጤን አስፈላጊ ነው' ብለዋል። ስትወጡ መውረድ እንዳለ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ መጓዝ ብቻ ሳይሆን ፍጻሜውን የሚያይ መሆን እንዳለበት አስምረውበታል። አዲሱ ራእይ “ኢትዮጵያ ያንተ ናት” ሲል ሐብታችንን ማወቅ፤ ሐብታችንን ማክበር፤ በሐብታችን መለወጥና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ዶክተር አብይ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ዋና ሀብት ሜዳ ሸንተረር፣ ወንዝ፣ ወርቅና ነዳጅ ሳይሆን ዜጎች እንደሆኑ አስገንዝበዋል። "ድንግል መሬታችን ስንል ከርመናል፤ መሬታችን ድንግል የሆነው ለእኛ ነው፤ አሁን ኢትዮጵያ ያልተደፈረው ድንግልናዋ የሰው ልጅ ጭንቅላት ብቻ ነው" ሲሉም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ። 'ያንን ጭንቅላት ስናውቅ፤ ስናከብርና ስንጠቀምበት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አለንና  ኢትዮጲያ ትለወጣለች' ሲሉ አመላክተዋል። ያለንን ሀብት ስናውቅ፣ ስናከብር፣ ስንጠቀምበትና ስንደመር ምን ያህል መለወጥ እንደሚቻል በአንድ ወር ውስጥ ማየት ችለናል ሲሉም አንጻራዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ሕዝቦች የአገሪቷን አንድነት መጠበቅና መከባበር የዕለት ከዕለት ተግባራቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። “ራዕይ የሌለው መሪ ነጂ እንጂ ፤ መሪ መሆን አይችልም” ያሉት ዶክተር አብይ፤ “አገሪቷ የሚጓዙበትን መስመር የተረዱና ተጠንቅቀው የሚራመዱ ባለ ራዕይ መሪዎች  ያስፈልጓታል” ብለዋል። የሀይማኖት አባቶችና እናቶችን፣ የመረጃ መሪ የሆኑ መገናኛ ብዙሃንን፣ የእውቀት መሪዎች መምሕራንን፣ ምሁራንና ተመራማሪዎችን፣ የጥበብ መሪዎችን፣ የሐሳብ መሪዎች የሆኑ ፈላስፋዎችን፣ የጤናና የሰላም መሪዎችን አድምጦና አክብሮ የሚራመድ መሪ ያስፈልጋል ብለዋል። በፍትሕና ሕግ መሪዎች የሚመራና እነርሱን የሚመራ ጠንካራ የፖሊሲ መሪ ያስፈልጋል ብለዋል። 'ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ለምን እንደሚሰሩ፣ ምን እንደሚሰሩ ጠንቅቀው የሚያውቁና ሙያቸውን የሚያከብሩ  መሪዎች ያስፈልጓታል' ብለዋል ዶክተር አብይ። ይህ መሆን ከቻለ የተጀመረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት በልጽጎ ወደፊት የሚደረገውን ግስጋሴ የሚያቆመው ኃይል እንደማይኖር ገልጸዋል። በዝግጅቱ ላይ የትውልድ ክፍተቶችን ማጥበብ በሚቻልበትና በአዳዲስ ሀሳቦች አስፈላጊነት ላይ ያጠነጠኑ ጽሁፎች ቀርበዋል። የትውልድ ክፍተት በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረበችው ደራሲ ሕይወት ተፈራ 'የታሪክ አረዳድ መስተካከልና አቀባበላችን እንደገና በበጎ መልኩ መቃኘት አለበት' ብላለች። በትውልድ መካከል የሚፈጠር ክፍተት ሊጠብና ሊጠፋ የሚችል በመሆኑ መደማመጥና መወያየትን ባሕል ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ደራሲዋ ገልጻለች። ታሪክና ትውልድ በሚል ጽሑፍ ያቀረበው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሙሉሸዋ በበኩሉ 'ታሪክ የሚፈጠርና የማይለወጥ በመሆኑ በልበ ብርሃንነትና በቀናነት ወደኋላ መመልከት ይጠቅማል' ይላል። "ማንም አገር በሰላም አልተመሰረተም" ያለው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሁሉም አገሮች በጦርነትና በትግል መመስረታቸውን ጠቅሶ፤ የጋራ የሆኑ በጎ ነገሮችን ይዞ እንደ አገር መቀጠል የተሻለና ዓለም አቀፋዊ እውነታ ያለው ክስተት እንደሆነ ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም