በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በድሬደዋ ከተማ ገቢ በመሰብሰብና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ረገድ አበረታች ውጤት ተገኝቷል - ከንቲባ ከድር ጁሃር

174

ድሬደዋ(ኢዜአ) ጥር 27/2015 በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በድሬ ደዋ ከተማ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ረገድ አበረታች ውጤት መገኘቱን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከዲር ጁሃር ገለጹ።

ከንቲባ ከድር ይህን የተናገሩት፤ የአስተዳደሩ ምክር ቤት 2ተኛ አመት 4ተኛ መደበኛ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ከንቲባው ገልጸዋል።

የታክስ እና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ገቢን ለማሳደግ የተከናወነው ስራ ለተሰበሰበው ገቢ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በስድስት ወራቱ የገጠር መሰረተ ልማቶችን የሚያሳድጉና የነዋሪውን የልማት ጥያቄዎች ይፈታሉ ተብለው ከተጀመሩ 117 ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች መካከል አራቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ነው ከንቲባ ከድር የገለጹት።

ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ 11 ሺህ 760 ስራ ፈላጊዎችን በመመዝገብ ለ7 ሺህ 12 ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ቋሚ የስራ እድል ያገኙት 2 ሺህ 1(2001) መሆናችውንና በቀሪው የበጀት ዓመት ወቅት ለቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራበት አመልክተዋል።

በተጨማሪም በጥቃቅንናና አነስተኛ የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ 183 ኢንተርፕራይዞች 58 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ነው ከንቲባው ያብራሩት።

ከዚህም ባለፈ ከ61 ሺ በላይ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ የልማት ተግባራት ተሰማርተው ከ26 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ስራ በማከናወን አስተዳደሩ ሊያወጣ የነበረውን በጀት አድነዋል ብለዋል።

የኑሮ ውድነት ችግርን ከማቃለል አንጻር ባለፉት ስድስት ወራት መሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች በስፋት መቅረብ መቻሉንም በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

በዚህም ከ6 ሺህ በላይ ስኳርና ከ19 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት ለማቅረብ ታቅዶ 4 ሺህ 800 ኩንታል ስኳርና ከአንድ ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ማቅረብ እንደተቻለም ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለጻ፤አስተዳደሩ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የፍትህ እና የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው ባከናወኗቸው ተግባራት 37 "ፀረ ሰላም አካላት" በቁጥጥር ስር ውለው ለሕግ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በስድስት ወራቱ በመንገድ ፣በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ በግብርና ፣በጤና፣በትምህርት በሌሎች ዘርፎችም አበረታች ስራ መከናወኑን አክለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በበኩላቸው አስተዳደሩ በውስን በጀት የሕዝብን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።

ይህም ተግባር በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም