በ 'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ሂደት አበረታች ውጤት እየታየበት ነው - ሚኒስትር መላኩ አለበል

202

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 27/2015 በ 'ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ሂደት ጥሩ ውጤት መታየት መጀመሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

በንቅናቄው አማካኝነት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢንዱስትሪው እየገቡ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የሸገር ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪ 'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በንቅናቄው አማካኝነት ሁሉም ክልሎች በተከናወኑ ስራዎች "ከፍተኛ ውጤት" ተገኝቷል ብለዋል።

የኤክስፖርት መጠን እና የስራ እድል ፈጠራ እድገት ማሳዩትን ገልጸው አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢንዱስትሪው እየገቡ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በንቅናቄው ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ሂደት ጥሩ የሚባል ውጤት እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ስራ አቁመው የነበሩ ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን ገልጸው አመራሩና ባለሀብቶች ባደረጓቸው ውይይቶች በርካታ ችግር መፍታት ተችሏል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅና ባለሀብቱም በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ እንዳሉት፤ ከተማው ካለው ምቹ ሁኔታ አንጻር የበርካታ ኢንዱስትሪዎች መገኛ ሆኗል።

ከተማው ለገበያ ቅርበት ያለው፣አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማት አውታሮች የተሟሉለት ስለሆነ ባለሃበቶች በብዛት በሚፈልጉት ዘርፍ ተሳትፈው ራሳቸውነና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር ተሾመ አክለውም "በከተማው ከሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል በስራ ላይ የሚገኙት 2 ሺህ ገደማ ብቻ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ 'የኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄም እነዚህን ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ለማስገባትና ያሉ እድሎች እንዲሁም ተግዳሮቶች ላይ ለመግባባት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት፣ የፋይናንስ ችግር፣የውጪ ምንዛሬ እጦትና የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር እየተፈተነው መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ አለመሆን እንዲሁም የኃይል አቅርቦትም ከፍተኛ ፈተና መሆኑን ገልጸው፤ ንቅናቄው በርካታ ችግሮችን ይቀርፋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የመንግስት አመራሮች እና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

የ ‘ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም