በባህርዳር ከተማ በስድስት ወር ከ18 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

235

ባህርዳር፣ ጥር 27 ቀን 2015 (ኢዜአ) የባህርዳር ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ለ18 ሺህ 191 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የአስተዳደሩ ሥራና ስልጠና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ነቢዩ ፈንታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሥራ ዕድሉ የተፈጠረው በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በግብርናና ሌሎች የሥራ መስኮች ነው።

የአስተዳደሩ ዓመታዊ ዕቅድ ለ46 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሥራ አጥ ለሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የተመዘገበው ውጤት የዕቅዱ 78 በመቶ እንደሆነ ገልጸው፤ ለዚህም 40 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን ጠቁመዋል።

እንደምክትል መምሪያ ኃላፊው ገለጻ፤ ቀደም ሲልና አሁን የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ከ21 ሺህ በላይ ወጣቶች የሙያ እና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

በቀሪው በጀት ዓመት ዕቅዱን ለማሳካትና የሥራ አጥ ቁጥርን ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት በጫማ ማምረት የሥራ እድል የተፈጠረላት ወጣት ንፁህ ይርጋ፤ "ዘመናዊ የወንድና የሴት ጫማዎችን ማምረት ጀምሬያለሁ" ብላለች።

ወጣቷ በቀጣይ ምርቶቿን ወደ ውጭ እስከመላክ የደረሰ ህልም ሰንቃ በመሥራት ላይ እንደሆነችም ተናግራለች።

የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ ከተመቻቸላት ከራሷ አልፎ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ህልም እንዳላት ገልጻለች።

በከተማ ግብርና የተሰማራችው ሌላኛዋ ወጣት ሰናይት አወቀ በበኩሏ፤ አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ወደ ሥራ መግባቷን ተናግራለች።

በባህርዳር ከተማ ባለፈው ዓመት 51 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም