በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከ152 ሺህ በላይ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዷል

138

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27/2015 በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከ152 ሺህ በላይ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገቡ መንግሥት መወሰኑን ተከትሎ እስካሁን ከ7 ሺህ በላይ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪ መሪ አስፈጻሚ ከድልማግስት ኢብራሂም ለኢዜአ እንደገለጹት በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ሥራ ላይ ለማዋል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ወደ ሥራ በማስገባት የታዳሽ ኃይልን ጥቅም ላይ ማዋልና የውጭ ምንዛሬ ወጪንም የሚያስቀር በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከውጭ ሳይገጣጠሙ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪናዎችን የጉምሩክ ታክስ 5 በመቶ ብቻ በመክፈል ከሌሎች የታክስ ክፍያዎች ነፃ ሆነው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከውጭ ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ይሆናል።

በመሆኑም በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከ152 ሺህ በላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ከድልማግስት ገልጸዋል።

በዕቅዱ መሰረት 148 ሺህ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውቶሞቢሎችና 4ሺህ 800 አውቶቡሶች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገቡ በያዝነው ዓመት መወሰኑን ተከትሎ እስካለፈው ታኅሳስ ወር ከ7 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ መግባታቸውን አስታውሰው፤ ይህም የነዳጅ ወጪን በመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪናዎችን መሰረተ-ልማት ለማሟላት በየቦታው ቻርጅ የሚያደርጉበት ጣቢያዎች (ስቴሽን) ለመገንባትና አገልግሎቱን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ለአገር ጥቅም ካለው የላቀ ፋይዳ ባለፈ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታና ሕዝብንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም