በአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ መረጃ አማካኝነት በድርቅ ሳቢያ ሊደርስ ይችል የነበረው የከፋ ጉዳት መቋቋም ተችሏል - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

322

አዳማ ኢዜአ ጥር 27/2015… በወቅቱ ተደራሽ በሆነ የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ መረጃ መሰረት በተከናወኑ ስራዎች በድርቅ ሳቢያ ሊደርስ ይችል የነበረ የከፋ ጉዳት መቋቋም መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

በአየር ትንበያው መሰረት ለቀጣይ ሶስት ወራት እንደሚዘገይ የተነገረውን የበልግ ዝናብ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል ብለዋል።

የበጋውን ወቅትና የመጪው የበልግ ወራት አየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

ውይይቱ የበጋውን ወቅት የአየር ሁኔታ ግምገማና የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ለመተንተን መዘጋጀቱ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገልጸዋል።

በመረጃው መሰረት በተደረገው ዝግጅት በዝናብ እጥረት ሳቢያ ያጋጠመውን ድርቅ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቋቋም መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ የተቀናጀ ርብርብ በመደረጉ ውጤታማ ተግባር እንዲከናወን ማድረጉን አመልክተዋል።

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ላይ ጉዳት ቢያደርስም በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላስከተለም ብለዋል ሚኒስትሩ።

በቀጣይ ሶስት ወራት የበልግ ዝናብ የሚዘገይ በመሆኑ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ዜጎች፣መንግስትና ባለድርሻ አካላት በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህም የውሃ እጥረት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የቤት እንስሳትን በቂ ውሃ ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች ማንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሩ መንግስት ሊያጋጥም የሚችለው ችግር ለመቋቋም ሀብት የማሰባሰብ ስራ እንደሚያከናውን በመጠቆም።

ከዚህም ባሻገር የኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም የውሃ ሀብት አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚዎች አካባቢ ተገቢ የሆነ ዝግጅት እንዲደረግ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ስራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአየር ሁኔታና ፀባይ መረጃን ለተጠቃሚዎች እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ያለፈው የበጋ ወራት የአየር ሁኔታ ከትንበያው ጋር የተጣጣመ መሆኑን አመልክተዋል።

የትሮፒካል ፓሲፊክና ሕንድ ውቅያኖስ ሙቀት መደበኛ ላይ በመሆኑ የበልግ ዝናብ ሊዘገይ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ተጠቃሚው ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት የሚሰጠውን የቅድመ ማስጠንቀቂያ የአየር ሁኔታ ትንበያን በመጠቀም ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር ለመቀነስና መቋቋም የሚያስችል ስራ በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ነው አቶ ፈጠነ ያስገነዘቡት።

በተለይ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አርሲና ባሌን ጨምሮ ደጋማው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም