1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት የመቱ-ጎሬ አየር ማረፊያ ግንባታ ተጀመረ

194

መቱ(ኢዜአ) ጥር 27/2015 በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚሰራ የተገለጸው የመቱ-ጎሬ አየር ማረፊያ ግንባታ ተጀመረ።

166 ሄክታር የሚያርፈው የአየር ማረፊያ ግንባታ በሶስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የአየር ማረፊያው ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ጫንቆ ግንባታውን በታቀደው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች በተለያዩ መስኮች የስራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የመንግስት አካላት እና ሕብረተሰቡ ለስራው ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግላቸው ስራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢሉባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው የአየር ማረፊያው ለዞኑ ማኅበረሰብ ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል ብለዋል።

ለአርሶ አደሩ የገበያ ዕድሎችን በማምጣት፣ የቱሪስት መዳረሻዎች የመጎብኘት እድላቸውን እንዲሰፋ የማድረግ እና ሌሎች ጠቃሜታዎችን እንደሚያስገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም