አልጄሪያ እና ሴኔጋል የቻን ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ይፋለማሉ - ኢዜአ አማርኛ
አልጄሪያ እና ሴኔጋል የቻን ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ይፋለማሉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27/2015 በሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) አስተናጋጇ አልጄሪያ እና ሴኔጋል ዛሬ ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታሉ።
የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰአት ከ30 እሰከ 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ይከናወናል።
የውድድሩ አስተናጋጅ አልጄሪያ በግማሽ ፍጻሜው ኒጀርን 5 ለ 0፤ ሴኔጋል ደግሞ ማዳጋስካርን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
አልጄሪያ በውድድሩ ያደረጋቻቸውን አምስት ጨዋታዎች አሸንፋለች። ዘጠኝ ግቦችን ስታስቆጥር ምንም ግብ አልተቆጠረባትም።
የበረሃዎቹ ቀበሮዎች ካስቆጠሯቸው ዘጠኝ ግቦች አምስቱን ያስቆጠረው የ25 ዓመቱ አጥቂ አይሜን ማሂኡስ ሲሆን የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በመምራት ላይ ይገኛል።
ሴኔጋል በቻን ውድድር ባደረገችው አምስት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፋለች።
የቴራንጋ አንበሶች ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ አንድ ግብ አስተናግደዋል።
አልጄሪያ እና ሴኔጋል የውድድርና ወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ለ23ኛ ጊዜ ተገናኝተዋል።
አልጄሪያ 14 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ሴኔጋል ደግሞ 4 ጊዜ አሸንፋለች። 5 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
ሁለቱ አገራት የቻን ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ይጫወታሉ።
በተያያዘ ዜና ትናንት በቻን ሻምፒዮና በተደረገ የደረጃ ጨዋታ ማዳጋስካር ኒጀርን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች።
ጂን ይቬስ ራዛፊንድራካቶ ለደሴቲቷ አገር ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
ማዳጋስካር በመጀመሪያ የቻን ተሳትፎዋ ስኬታማ የሚባል ጉዞን ማድረግ ችላለች።
የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር መሆኑ ይታወቃል።