በከተሞች ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመቆጣጠር ዘመናዊ የመሬት አያያዝ መረጃ ሥርአት ትግበራ እየተከናወነ ነው

155

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 26/2015--በከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ የመጣውን ህገወጥ የመሬት ወረራ ለመቆጣጠር ዘመናዊ የመሬት አያያዝ መረጃ ሥርአት ትግበራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

"ከተሞችን የለውጥና የብልጽግና ማዕከል እናደርጋለን'' በሚል መሪ ሃሳብ የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ያዘጋጀው የአጋር አካላት የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ፈንታ ደጀን እንደተናገሩት የክልል ከተሞች የመሬት አስተዳደር ስርአት በዘመናዊ የመረጃ ስርአት ባለመደራጀቱ ለህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተጋለጠ ነው።

"ዘመናዊ የካዳስተር ስርአት በከተሞች የሚስተዋለውን የመሬት ወረራ ለመቆጣጠርም ሆነ ሀብቱን በአግባቡ ለማስተዳደር ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

አቶ ፈንታ እንዳሉት በሀገሪቱ አነስተኛ፣ መከካለኛና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው 2ሺህ 500 ከተሞች ያሉ ሲሆን፣ ከተሞቹ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወኑ ናቸው።

"በቀጣይ ዓመትም በጥናት ተለይተው በተመረጡ ከተሞች የካዳስተር ወይም ዘመናዊ የመሬት አያያዝ የመረጃ ስርአት ትግበራ በትኩረት ይሰራል" ሲሉም ጠቁመዋል።

"ከሀገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ገቢ እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን የሚያመነጩት ከተሞች ናቸው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከተሞችን በዕቅድና በፕላን እንዲመሩ በማድረግ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ መደገፍ እንደሚገባም አስረድተዋል።

"የከተሞችን የሕዝብ ቁጥር እድገት ከግብርናውና ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር አድገታቸውን ለማፋጠን እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢያዝን እንኳሆነ ናቸው።

የከተሞች የህዝብ ቁጥር እድገት በጥበብ ከተመራ ለኢንዱስትሪው በቂ የሰው ሀይል ለማቅረብና ለቴክኖሎጂ አቀባበል የተመቸ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ የከተሞች ቁጥር በ2001 ዓ.ም ከነበረው 231 በአሁኑ ወቅት ወደ 681 ማደጉን ጠቁመው፤ በአማካይ በየዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ለተሻለ ኑሮና ሥራ ፍለጋ ወደ ከተሞች እንደሚገባ አስረድተዋል።

"ከተሞች ለነዋሪዎች የተሟላ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እራሳቸውን በገቢ ከማጠናከር ጀምሮ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ያሉ ውስንነቶችን ፈተው እድገታቸውን ለማፋጠን ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማም ከተሞች ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት የነዋሪዎቻቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍታት የሚችሉበትን አሰራር ለመዘርጋት መሆኑንም አቶ ቢያዝን አስረድተዋል።

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የከተሞች መስፋፋት ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ከተሞችን በፕላንና በዕቅድ ለመምራት የተጠናከረ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።

እንደ አቶ ባዩህ ገለጻ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት አሰጣጥ አለመኖር፣ የቤትና የመሬት አቅርቦት ችግር፣ የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጉድለት እንዲሁም ብቃት ያለው የከተማ አመራር አለመኖር በከተሞች የተስተዋሉ ተግዳሮቶች ናቸው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች ተሳታፊ ሲሆኑ የቢሮው የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸምም ይገመገማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም