ባህልን በመንከባከብና በማሳዳግ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ማዋል ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

133

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 26/2015 ባህልን በመንከባከብና በማሳዳግ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ማዋል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ ።

14ተኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል "ባህሎቻችን የአንድነታችን ካስማ ናቸው" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት የባህል ፌስቲቫል ባህልን ለማጠናከር፣ ገፅታን ለመገንባት እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲውል እየተሰራ ያለው ስራ ሊጠናከር ይገባል ።

በተለይ ያሉንን ባህሎች በመንከባከብና በማሳደግ ቱሪስቶች እንዲጎበኟቸው በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በማድረግ ተጠቃሚነታችንን ማስፋት ይገባል ሲሉ አክለዋል።

በዚህም በባህል ፌስቲቫሉ እርስ በእርስ በመተዋወቅና በመቀራረብ የአዲስ አበባን ሰላም ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ስላለው ሁሉም ይህን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ያሉንን ባህላዊ እሴቶች ለሰላምና ለአብሮነት በመጠቀም ለትውልድ ማሻገር ይገባል ብለዋል።

እየተከናወነ የሚገኘው ፌስቲቫልም ነባር ባህላዊ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው በበኩላቸው ነባር ባህሎችን መሠረት እንደያዙ እንዲቀጥሉ የሁሉም ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በተለይ ተቋማት የንድፈ ሀሳብና የክህሎት ሥልጠና መስጠት፣ የባህል ጥበባት ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግና ለቱሪዝም ግብዓት እንዲሆኑ መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል ።

14ተኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ከጥር 26 እስከ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም