አገር በቀል ምርጥ ዘርን ከሌሎች አገራት ዝርያዎች ጋር ማዳቀልን የሚፈቅድ አሰራር የያዘ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

182

አዳማ (ኢዜአ) ጥር 26/2015 አገር በቀል ምርጥ ዘርን ከሌሎች አገራት ዝርያዎች ጋር ማዳቀልን የሚፈቅድ አሰራር የያዘ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።

ማሻሻያው የውጭ ኩባንያዎች ጭምር በዘር ብዜት እንዲሳተፉ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ምርት አምራችን እና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን በተዘጋጀ የረቂቅ አዋጅ እና የምርጥ ዘር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ በአዳማ ተካሄዷል።


የግብርና ምርት አምራችን እና አስመራች ግንኙነትን መወሰኛ ረቂቅ አዋጅ አዲስ የተረቀቀ የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነ ተነግሯል።


የምርጥ ዘር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከ2005 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ እየሆነ ያለውን ነባር አዋጅ እንደሚተካ ተጠቁሟል።


የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የምርጥ ዘር ማሻሻያ አዋጁ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ጭምር በዘር ብዜት እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በምስራቅ አፍሪካ በተለይ ኬንያና ታንዛንያ ላይ የተዘጋጀው ምርጥ ዘር ለኢትዮጵያ የአየር ጠባይ ይስማማል ወይስ አይስማም? የሚለውን በመለየት የተሻሉ ዝርያዎች ማዳቀልን እንደሚፈቅድ ተናግረዋል።


አርሶ አደሩ የተሻሻለ ዘር መጠቀሙ “ከ20 እስከ 30 በመቶ የምርት ዕድገት ያመጣል” ብለዋል።


በሌላ በኩል የግብርና ምርት አምራችን እና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለገበያ ከማቅረባቸው በፊት ቀድመው ከአምራች ጋር ውል ማሰር የሚያስችላቸው እንደሆነም ነው ዶክተር ግርማ የገለጹት።


ይህም አርሶ አደሩ ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙትን ችግሮች እንደሚፈታ ተናግረዋል።

አዋጁ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳግ ከመሆኑም ባለፈ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት መልኩ ምርት በጥራትና በብዛት እንዲመረት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም ገዢ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲመረት የቴክኒክ ድጋፍ፣የብድር አገልግሎትና የሌሎች ግብዓት ድጋፍ የሚሰጥበትን አማራጮች እንዲዘረጉ ያደርጋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።


በአጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ ለአምራች፣ለአስመራች እና ላኪ የጋራ ዋስትና እንደሚሰጥም አመልክተዋል።


ረቂቅ አዋጆቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽድቆ ከ2016 ዓ.ም አንስቶ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል።


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው የውል ግብርና እርሻን ለማስፋፋት እንዲሁም አርሶ አደሩ ምርቱን በጥራትና በብዛት እንዲያመርት የሚያስችል ነው ብለዋል።


የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እስከ አሁን በተከናወኑ ስራዎች የወጪ ምርቶችን ከማሳደግ ባለፈ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በመተካት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።


የምክር ቤት አባላት ወደ ሕዝቡ ለእረፍት ሲመለሱ ረቂቅ አዋጆቹን በማወያየት ተገቢውን ግብዓት ማሰባሰብ እንደሚገባቸው ምክትል አፈ-ጉባኤዋ አሳስበዋል።


የዛሬው ውይይት በረቂቅ አዋጆቹ ግብአት ማሰባሰብን አላማ ያደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም