የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝበ-ውሳኔው በሰላም እንዲካሄድ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

183

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 26 ቀን 2015 የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ሰላማዊ ሆኖ እንዲፈጸም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታወቀ።

ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የሕዝበ- ውሳኔው በኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ ዞኖች እና ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

ህዝበ ውሳኔው በሚካሄድባቸው 3ሺህ 752 ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጡ ሰላማዊ እንዲሆን ፖሊስ በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው 3 ሚሊዮን ህዝብ በዕለቱ በሰላም ድምፅ ሰጥቶ እንዲመለስ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የፀጥታ ኃይል ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ዓለማየሁ አክለውም "ቀደም ብሎ ከተካሄዱት ከሲዳማና ከደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ህዝበ ውሳኔ በቂ ልምድ ቀስመናል" ብለዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝበ ውሳኔው ጋር ተያይዞ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የህግ ማስከበር ስራ እንዲሰራ በምርጫ መመሪያዎች ዙሪያ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ቀደም ሲል ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከምርጫ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ተግባራትን የሚያጣራ ራሱን የቻለ የምርመራና የመረጃ ቡድን ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር በልዩ ሁኔታ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር ትስስር መፈጠሩን ገልጸው፤ በተለይ ኮሚሽኑ ከክልሉ ልዩ ኃይል፣ከመከላከያና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንዲወጣ ቀደም ሲል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት መካሄዱን ኮሚሽነር ዓለማየሁ ገልፀዋል።

ፖሊስ ህዝበ ውሳኔው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት ህዝቡ ከጎኑ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ኮሚሽነር ዓለማየሁ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም