የማይቻል የሚመስል ግን የሚቻል

158

(ኤልያስ ጅብሪል)

የአፍሪካ መሪዎች፣ የልማት አጋሮቿ እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ አርሶ አደሮች ሴኔጋል “ዳካር“ ከተማ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ጉባዔ አካሂደዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ አዘጋጅነት ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባዔ በተለይም የአህጉሪቱን የምግብ ምርት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲመክሩ ቆይተዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አክንውሚ አዴሲና እንዳሉት፤ እንደ አጠቃላይ ዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መሆኗ የጉባዔውን አስፈላጊነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

አፍሪካ በምግብ ራሷን ለመቻል ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ምግብ በመለመን ኩራት የለምና አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል እየተሰማኝ ነው “ በማለት ጠንክሮ መስራት ከተረጂነት ለመላቀቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አፍሪካ ከውጭ በሚመጣ ምርት ላይ ያላት ጥገኝነት ማብቂያው አሁን መሆን እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

አፍሪካ የዓለምን ህዝብ መመገብ የሚያስችል በቂ የእርሻ መሬት ቢኖራትም ከ100 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ከውጭ ለማስመጣት በየዓመቱ 75 ቢሊየን ዶላር እንደምታወጣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት አመላክቷል።

ነገር ግን በአንድ በኩል አፍሪካውያን አህጉራቸውን አልምተው መበልጸግ እንደማይችሉ የሚያስቡ አካላት ጥቂት ባለመሆናቸው በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አስተሳሰብ በአፍሪካውያን ዘንድም ጭምር በመስፋፋቱ እና በሌሎችም አያሌ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት አፍሪካ በልኳ ሳትለማ ቆይታለች።

በዚህም ሚሊዮኖች አፍሪካውያን ለረሃብ ስቃይ የተዳረጉ ሲሆን፤ የአፍሪካ ቀንድ አገራትና ማዳጋስካር ለዚህ ተጠቃሽ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል። በአገራት መካከል የሚስተዋሉ ግጭቶች ይበልጥ ችግሩን እያባባሱት እንደሚገኙም ተብራርቷል።

Senegal and African Development Bank hosts food summit

በጉባዔው የተገኙት የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት መሐሙድ ቡሐሪ እንደገለጹት፤ ራስን የመቻሉን ጥረት ለማሳካት የአፍሪካ አገሮች ለግብርና እና ለገጠር መሠረተ-ልማት የሚያውሉትን የገንዘብ መጠን ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ለአርሶ አደሩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ እንዲሁም አፍሪካውያን የገጠሩን አካባቢ ይበልጥ በማልማት ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት መቀነስ እንደሚያስፈልግ በጉባዔው ተመልክቷል።

ድርቅንና ረሃብን በእጅጉ ለመቀነስም በመስኖ ሥራ ላይ ከፍ ያለ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ የተጠናከረ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አቅጣጫ ተቀምጧል።

በግብርና ምርት ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ የግብርና የመድህን ዋስትና ሊቀንሰው እንደሚችል እንደመፍትሔ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

አፍሪካ እንደ አህጉር ያላትን የተፈጥሮ ኃብት በሚገባ በመጠቀም ከራሷ አልፋ ሌሎች አህጉራትን ልትመግብ የምትችልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውም ነው የተገለጸው።

በጉባዔውም ለልምድ ልውውጥ ይረዳ ዘንድ አገራት በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገቡትን ስኬት ዘርዝረዋል።

ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የስንዴ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ የምታመርት አገር መሆኗ ተጠቅሷል። በዚህም ታመርት የነበረውን የአየር ሙቀት መቋቋም የሚያስችል የስንዴ ዝርያ በአራት ዓመት ከ5ሺህ ወደ 800 ሺህ ሄክታር ከማስፋፋቷም በላይ ከስንዴ ላኪ አገራት መካከል ለመመደብ እንደሚያስችላት ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በእርዳታ የምትቀበለውን ስንዴ ጨምሮ በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ታስገባለች። ለዚህ የስንዴ ግዥም በየዓመቱ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

ራስን በምግብ ከመቻል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በስፋት የስንዴ ምርት ልማት ውስጥ ገብታለች።

በበጋ ስንዴ ልማት አርሶ አደሮች በመስኖ እንዲያመርቱ እያለማመደች ለጎረቤት አገራት ጭምር በምሳሌነት ተጠቃሽ ሆናለች። በዚህም በዓይን የሚታይ በተግባር የታገዘ የስንዴ ምርት ስኬትን እያስመዘገበች ትገኛለች።

በዚህም እንቅስቃሴዋ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ጭምር እውቅና ተችሯታል። ይህንንም ስኬት በዓለም አቀፍ መድረክ ከመሰከሩት መካከል የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አክንዊሚ አዲሲና ተጠቃሽ ናቸው።

“ ኢትዮጵያ ከዚህ በኃላ በስንዴ ሸመታ ላይ የማትመለከቷት አገር ትሆናለች፤ በከፍተኛ ደረጃም የሰበሰበችውን የስንዴ ምርት ጎረቤቶቿን ለመመገብ እየተሰናዳች ነው” በማለት ነበር የተናገሩት።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2023 ለስንዴ ግዥ የውጭ ገበያ እንደማትመለከትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር በነበራቸው ውይይት አረጋግጠውላቸዋል።

ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት ዘመቻ በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት የሚያፋጥን ሌላው ማሳያ እንደሆነም ነው የሚጠቀሰው።

ይኸው መርሃ-ግብርም ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚተገበር ሆኖ፤ ግቡም የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የምግብ ሥርዓትን ማሻሻል ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የወጪ ንግድ ገቢን የማሳደግና ከውጭ የሚገባ የእንስሳት ተዋፅኦን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያለመ ነው።

ሌላው በምግብ ራስን ከመቻል ጋር የሚነሳው ኢትዮጵያ በከተሞች ደረጃ እያካሄደች ያለችው የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ ነው። በዚህም ሰፊ ዘመቻ የከፈተችበትና ሕብረተሰቡን በማስተባበር ወደ ተግባራዊ እርምጃ በመግባት ቆርጣ የተነሳችበት አንዱ አቅጣጫ ነው።

በቅርብ ጊዜ ከተደረጉ ጥናቶች በመነሳት በከተሞች የሚገኙ 10 በመቶ የአረንጓዴ ሥፍራዎችን ተጠቅሞ የከተማ ግብርና በማከናወን 15 በመቶ የምግብ ፍላጎትን መሸፈን እንደሚያስችል ይጠቁማሉ።

በተለይም የከተማ ነዋሪዎች ባላቸው አነስተኛ ሥፍራ ወይም ጠባብ ቦታ ላይ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ከራስ አልፎ ሌሎችንም ለመደገፍና የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታል።

በዚህም ነዋሪዎች በግለሰብም ሆነ በማህበር በመደራጀት በአቅራቢያቸው በሚያገኙት ክፍት ቦታዎች ለምግብነት የሚያገለግሉ ምርቶችን በማምረት በገቢ ራሳቸውን መደገፍ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህም በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ የሚያግዝ ነው።

ከዚህ ባሻገር ድርቅን መቋቋም የሚያስችል የበቆሎ ዝርያ ምርት በኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ከእጥፍ በላይ መድረሱ እንደ አህጉር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንደሚሆን አመላካች መሆኑ በጉባዔው ተገልጿል።

በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ በዓለም ላይ እያደረሰ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም አገራቸው የራሷን ማዳበሪያና ስንዴ ማምረት መጀመሯን የተናገሩት ደግሞ የዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ናቸው።

ለዚህም አፍሪካውያን ያሉባቸውን ችግሮች ሌሎች ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ በራሳቸው መፍታት የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ማመቻቸት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአፍሪካን በምግብ ራስን መቻል አስመልክቶ በመሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ፣ የግል ክፍለ-ኢኮኖሚው ምርታማነት እንዲዳብር ተጋግዞ መሥራት አዋጭ መሆኑም ተጠቁሟል።

የግብርና ውጤቶች፣ የወተት ተዋፅኦ፣ የዓሣ ልማትና የመሳሰሉት ወቅቱ የሚፈቅደውን ቴክኖሎጂ በማጣመር ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅም እንዲሁ።

መሠረተ-ልማቶችን ማሟላት፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እና የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ውጤቶችን ወደ ገበያ በማምጣትና ተወዳዳሪ በመሆን የአገራቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ተሰጥቶታል።

የአፍሪካ አገራት እነዚህንና ሌሎች ልምዶችን ወደ ተግባር ለውጠው በትብብር ከሰሩ የማይቻል የሚመስለውን ከተረጂነት መላቀቅና ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍን እውን ማድረግ ይችላሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት የጀመሩት ውጤታማ የልማት እንቅስቃሴ ደግሞ አፍሪካውያን በርግጥም በምግብ ራሳቸውን የሚችሉበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አመላካች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም