እየተገነቡ ባሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች ጥያቄዎቻችን እየተፈቱ ነው- የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች

153

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ጥር 26/2015 ከለውጡ ወዲህ እየተገነቡ ባሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች የረዥም ጊዜ ጥያቄዎቻቸው እየተፈቱላቸው መሆኑን በሶማሌ ክልል የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማው የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሀ፣ የመንገድና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ለከተማዋ ልማትና እድገት አስተዋጾ ማድረጋቸውን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል ።

ከነዋሪዎቹ መካከል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ሱልጣን ቃሊብ ዲኢስ አብዲ እንደገለጹት ጎዴ ከተማ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ሰላማዊና ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይባት ሆናለች።

“ከለውጡ በፊት የማይታሰብ የነበረው የህንፃ ግንባታ ስራ አሁን በየትኛውም የከተማዋ አቅጣጫ ሲገነባ ይታያል” ያሉት ሱልጣን ቃሊብ እየተገነቡ ያሉ ህንጻዎች ለነዋሪው የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ለከተማዋ ውበት እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

“ከለውጡ ወዲህ በከተማዋ በሁሉም መስክ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው “ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አርዱ አህመድ ናቸው።

"በከተማዋ የተገነቡ አስፓልት መንገዶችና የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች የነዋሪውን የዘመናት ጥያቄ የመለሱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

ከዋቢ ሸበሌ ወንዝ ተጠልፎ የተገነባ የከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም የነዋሪውን ችግር የፈታ መሆኑን አመልክተዋል።

“ከለውጡ በፊት የነበሩት የሰላምና ደህንነት ስጋቶች ተወግደው የህዝብ ተጠቃሚነት ሰፍኗል፤ በዚህም ደስተኞች ነን” ያሉት ደግሞ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ከድር አብዲሳ ናቸው።

በህዝቡና በአመራሩ መካከል መተማመንና መቀራረብ በመፈጠሩ ከተማዋ በፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

ሌላው የሀገር ሽማግሌ ሱልጣን አብዲ ቃሲም ኡላድ በበኩላቸው በህዝቡና በአስተዳደሩ መካከል መግባባት በመፈጠሩ በከተማዋ ፈጣን ልማት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል ።

“እጅ ለእጅ ተያይዘን የመጣውን ልማት እናስቀጥላለን “ ሲሉም አመላክተዋል ።

የጎዴ ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ኢሳቅ በበኩላቸው ካለፉት አራት አመታት ወዲህ በከተማዋ በንጹህ መጠጥ ውሀ፣ በመንገድና በሌሎች አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች ግንባታ አበረታች ለውጥ መፈጠሩን ተናግረዋል ።

በተለይም በመንግስትና በአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 475 ሚሊዮን ብር ወጭ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት የህዝቡን የአመታት ጥያቄ የፈታ መሆኑን አመልክተዋል ።

የውሀ ተቋሙ በ24 ሰዓት 9ሺህ 600 ሜትር ኪዩብ የተጣራ ንጹሕ ውሃ በማምረት ህዝቡ በቂ ውሃ እንዲያገኝ ከማድረጉም በተጨማሪ በከተማዋ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም