የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የተጀመረውን ፈጣን የለውጥ ጉዞ በማፋጠን ለላቀ ውጤት ልንተጋ ይገባል--ከንቲባ አዳነች አቤቤ

237

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 26/2015 የህብረተሰቡን ፍላጎትና ጥያቄዎች ለመመለስና የተጀመረውን ፈጣን የለውጥ ጉዞ ከእስካሁኑ በበለጠ ፍጥነትና ትብብር በማስቀጠል ለላቀ ውጤት ልንተጋ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የ2015 የመጀመርያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ “ባለፉት ስድስት ወራት በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፍንም በርካታ ውጤታማ ስራዎች ማከናወን የቻልንበትና እቅዶቻችንን ለመፈፀም የታየው ትጋትና ተነሳሽነት አበረታችና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያየንበት ነበር” ብለዋል ።

በተለይ የተቋም ሪፎርም ስራችን አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የስራ እድል በመፍጠር ለውጥ የሚያመጡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመልካም አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ ገምግመናል ነው ያሉት።

ከንቲባ አዳነች አክለውም የህብረተሰቡን ፍላጎትና ጥያቄዎች ለመቅረፍና የተጀመረውን ፈጣን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ከእስካሁኑ በበለጠ ፍጥነትና ትብብር ለላቀ ውጤት ልንተጋ ይገባል ብለዋል፡፡


ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በቁርጠኝነት በመታገል ፣ተቋማዊ አቅም በማጠናከር ፣የሪፎርም ስራዎችን በማከናወንና የመፈፀም አቅምን ከፍ በማድረግ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡


አዲስ አበባን ውብና ለነዋሪዎቿ የምትመች ፣ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖችን በላቀ ሁኔታ የምትደግፍ ፤ መደጋገፍ የሰፈነባት እንድትሆን የተጀመረው ጥረት ከህዝቡ ጋር በመሆን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም