በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የአፍሪካ ኢኮኖሚ በ3 ነጥብ 8 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል የተ.መ.ድ ትንበያ አመላከተ

123

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የአፍሪካ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በ3 ነጥብ 8 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትንበያ አመልክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የአህጉሪቷ የዘንድሮ ኢኮኖሚ እድገት ከአምናው 4 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ማለቱ ተገልጿል።

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የ2022 የዓለም ኢኮኖሚ አፈጻጸምና የ2023 የዓለም ኢኮኖሚ ትንቢያ የተመለከተ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። 

የዓለም ኢኮኖሚ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሂደት በማገገም ላይ በነበረበት፣ የዩክሬንና የሩስያ ጦርነትና ድርቅ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ተመላክቷል። 

እንዲሁም የምግብና የኃይል እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መኖር፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም ክስተቶች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ተገልጿል። 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የማክሮ ኢኮኖሚክስና አስተዳደር ክፍል ዳይሬክተር አደም አልሂራይካ በሰጡት ማብራሪያ፣ የዓለም ኢኮኖሚ ባልተጠበቁ ክስተቶች እየተፈተነ ይገኛል ብለዋል። 

በተለይም የአፍሪካ አህጉር የዋጋ ግሽበት መባባስ፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመርና ሌሎች ችግሮች ኢኮኖሚው ላይ ጫና ያሳድራሉ ብለዋል። 

የኢንቨስትመንትና የኤክስፖርት ምርቶች ማነስ ሌላኛው የኢኮኖሚው ፈተና መሆኑን በመጠቆም። 

በዚህም የተነሳ የአህጉሪቷ የዘንድሮ ኢኮኖሚ እድገት 3 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚሆንና ይህም አምና ከነበረው 4 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል።  

ምዕራብ አፍሪካ 2 ነጥብ 3 በመቶ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ 2 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል ነው ያሉት።  

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በርካታ የምዕራባውያን አገራት ከሁለት በመቶ በታች ዕድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የእስያ አገራት የተሻለ ዕድገት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም