በሰሜን ወሎ ዞን አምስት ወረዳዎች የወባ በሽታ የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

70
ወልዲያ መስከረም 25/2011 በሰሜን ወሎ ዞን አምስት ወረዳዎች የወባ በሽታ የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡ ሥራው በተለይ ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ በተጋለጡት ራያና ቆቦ ወረዳዎች አትኩሯል። በመምሪያው የወባና ሌሎች ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከላከያ ባለሙያ አቶ ጥላሁን ገብረ ሕይወት ሥራው እየተካሄደ ያለው የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ለበሽታው ተጋላጭነት ባለባቸው ወረዳዎች መሆኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። በሽታው በተለይ በራያና ቆቦ ወረዳዎች ለበሽታው በተጋለጡ ቀበሌዎች የሚኖር ሕዝብ እያሳተፈ መሆኑንም ገልጸዋል። ለዚህም “ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ ለወባ መራቢያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩትን የተቋቱ የውሀ ቦታዎችን የማፋሰስ፣ የማዳፈንና የመጠቅጠቅ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል” ብለዋል፡፡ እንዲሁም ለወባ ትንኝ መራቢያነት አመቺነት ያላቸውን ቁጥቋጦዎችንና በአረም የተሞሉ ቦታዎችን መጽዳታቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይም ከፍተኛ የወባ ስርጭት በሚታይባቸው ራያና ቆቦ ወረዳዎች 11 ቀበሌዎች ውስጥ 551 ኪሎ ግራም ጸረ ትንኝ ኬሚካል  መረጨቱን ባለሙያው አስታውቀዋል። በዚህም 11ሺ190 ቤቶችን በመሸፈን ከ39ሺህ በላይ ሕዝብ ከበሽታው መጠበቁን አመልክተዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ዓመት 2ሺ445 ሰዎች በወባ ተጠቅተው ህክምና ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በዘንድሮው ክረምት የታማሚዎች ቁጥር 1ሺህ 487 መውረዱ ስርጭቱ እየቀነሰ መምጣቱን በማሳያነት አቅርበዋል። በጤና ኬላዎች ቀላል የመመርመሪያ መሳሪያዎች በመሰራጨታቸው በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ መከሰቱ እንዳቆመ አቶ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡ በጉባ ላፍቶ ወረዳ የቀበሌ አራት ነዋሪ አርሶ አደር ጌታቸው አበራ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የወባ በሽታ ለውሃ ማሰባሰቢያ የሚጠቀሙበትን ኩሬ የውሃ ስርገት መከላከያ(ጂኦሜምብሬን)በማልበስና በየጊዜው ውሃውን በማንቀሳቀስ የወባ ትንኝ ተረጋግታ እንዳትራባ እያደረጉ ነው፡፡ የአልጋ አጎበርን በመጠቀም እርሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በመጠቀም በሽታውን  እንዲቀንስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ ሰባት ነዋሪ አርሶ አደር መንገሻ አያሌው በበኩላቸው ከአካበቢያቸው የወባ መራቢያ ሥፍራዎችን ያጸዱ  ሲሆን፣ በቤታቸው የኬሚካል ርጭት እንደተከናወነላቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም