የ 71 ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ ሊካሄድ ነው

171

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥር 25/2015 በጦርነቱ የወደሙ 71 ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ መገባቱን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በዚህም የ71 ትምህርት ቤቶች የግንባታ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በዛሬው እለት ተካሂዷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ በበጀት ዓመቱ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማር ሥራ ክፍት ይደረጋሉ።

በበጀት ዓመቱ 5 ትምህርት ቤቶች በዲያስፖራ ትረስት ፈንድ፣ 16 ትምህርት ቤቶች በሰዎች ለሰዎች ድርጅት 50 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዓለም ባንክ የገንዘብ ትብብርና ድጋፍ ግንባታቸው እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 13 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ተገልጿል።

ደረጃቸውን የጠበቁና ለትምህርት ምቹ የሆኑ መማሪያዎችን መገንባት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የግንባታውን ኃላፊነት የሚወስዱ ተቋራጮች ፕሮጀክቱ ያለውን አገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ በትጋትና በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ትምህርት ቤቶች ትውልድ የሚቀረጽባቸውና አገር የሚገነባባቸው መሆኑን በመረዳት በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለባቸው በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሚኒስትሩ የትምህርት ፕሮግራም ጥራት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ወጋሶ በበኩላቸው በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት መሉ ለሙሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶች በተሻለ መንገድ መገንባት የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች አካል ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ከማህበረሰቡ፣ አጋር የልማት ድርጅቶች፣ በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከመንግሥት ኃብት በመሰባሰብ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እስከ አሁን በአጠቃላይ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ሃብት መሰብስብ መቻሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ የሥራ ተቋራጮች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማሳሰብ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም