የሰላም ስምምነቱ መንግሥት የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ነው -የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

151

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 25/2015--- የሰላም ስምምነቱ መንግሥት የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ገለጹ።

"ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልፅግና ጉዟችን ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ የሰላም ስምምነቱ መንግሥት የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ነው።

"ጦርነቱ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ጥፋት ቢያስከትልም በሰላም ስምምነት መቋጨቱ እንደ ሀገርና ህዝብ የሚጠቅምና የተሻለ አማራጭም ነው" ብለዋል።

በተለይ በሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ተደቅኖ የነበረውን የስጋት ዳመና የቀለበሰ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካላት ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ አንጻር የተለያዩ ፍላጎቶችና ጫና እንዳለባት ጠቁመው፣ ጥቅሟን የምታስጠብቅበት ስትራቲጂያዊ አሰራር መከተል ግድ የሚላት መሆኑን ገልጸዋል።

"ከሃይል ይልቅ የሰላም አማራጭ መከተል ጠቀሜታው የጎላ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፣ የሰላም ስምምነቱ ያካተታቸውን ጉዳዮች ለህዝብ በግልፅ ከማሳወቅ ጀምሮ አተገባበሩን በማስገንዘብ ረገድ መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

"ህዝባዊ ውይይቱ ሀገራዊና ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ሀገር የመገንባት ጉዞና ዓላማን ለማሳካት እንዲቻል ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው" ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ናቸው፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በርካታ ፈተናዎችን በመሻገር ሀገራችን ስትመራበት የነበረውን ከፋፋይ ትርክት በአዲስ ትርክት ለመቀየር መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ፖለቲካዊ መሰረቶች መጣላቸውን ነው ያመለከቱት።

"ፅንፈኝነት እንዲያድግ፣ እንዲበቅልና ዛሬ ላይ ልዩነትን ወደሚያባበስ ደረጃ እንዲሻገር በማድረግ የተፈጠረውን የአስተሳሳብ ዝንፈት ለማስተካካል ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው" ብለዋል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ወንድማማችነት፣ አብሮነት፣ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት የሚለው መሪ ሃሳብ በአዲስ መነሻ አስተሳሰብ የለውጥ መሳሪያ በማድረግ ጥሩ መሰረት እየተጣለ መሆኑንም አቶ አዲሱ አስረድተዋል።

"የመድረኩ ተሳታፊዎች ያነሷቸውን መንግስት በግብዓትነት ወስዶ በቀጣይ ልማቱንና ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ይጠቀምባቸዋል" ሲሉም ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው፣ የፀጥታ አካላትና ህዝቡ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ህልውናዋ ፀንቶ እንድትቀጥል ማድረጉን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ አሁን የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

"ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች ለከተማ አስተዳደሩ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ጠቃሚ ግብዓቶች ናቸው" ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ ከህዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች በቀጣይም ተጠናከረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች አቶ ጌጡ ታደሰ እንዳሉት በከተማው የሚስተዋሉ የኑሮ ውድነት፣ የወጣቶች ስራ አጥነትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራል፣ የክልልና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም