ጠንካራና ዘመናዊ ሠራዊት በመገንባት ሂደት የመከላከያ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው- የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ

220

አዲስ አበባ ጥር 25 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ ጠንካራ ሠራዊት በመገንባት ሂደት የመከላከያ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ እየተወጡ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ በዘመናዊ ወታደራዊ ሙያ /ፕሮፌሽናሊዝም/ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የውይይቱ ዓላማ በአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት ቀጣይነት ያለው የሪፎርም ሥራ ለማከናወን ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑ ተገልጿል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከለውጡ በፊት በሚኒስቴሩ የነበሩ መዛነፎችን በለውጥ ሥራዎች የማስተካከል ሥራ ተከናውኖ መከላከያ ኢትዮጵያን በሚመስል መልኩ ተገንብቷል ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ ጠንካራና የዘመነ የአሠራር ሥርዓት ከተዘረጋባቸው ተቋማት መካከል መከላከያ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የተለያዩ አገሮች የጥቅም፣ ፍላጎት፣ የሰላምና መረጋጋት ፈተና የሚስተዋልበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የሚችል ዘመናዊና ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቷ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በመከላከያ ሠራዊት ሥር የሚገኙ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁልጊዜ የሚማር፣ የተማረውን በተግባር የሚፈጽምና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የታጠቀ ጠንካራና ብቁ ሠራዊት መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደመቀ መንግሥቱ፤ ኮሌጁ ከተመሰረተበት 1998 ዓ.ም ጀምሮ በአራት የትምህርትና የሥልጠና ፕሮግራሞች በርካታ መኮንኖችን አሰልጥኖ በማውጣት በዘርፉ የላቀ ብቃት እንዲኖራቸው አስችሏል ብለዋል።

ከሚሰጠው ትምህርትና ሥልጠና በተጨማሪ በምርምር ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኮሌጁ በተቋሙ ለተጀመረው የፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የጦር አዛዦች፣ የቀድሞው የሠራዊት አባላት በተሳተፉበት መድረክ ዘመናዊ ሠራዊት የመገንባት ሂደትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም