የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት ከ568 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ

255

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የፖስታ ትራፊክ በማንቀሳቀስ ከ568 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሃና አርአያሥላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለማግኘት አቅዷል።  

ይህንንም ተከትሎ በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ከአምስት ሚሊየን በላይ የፖስታ ትራፊክ በማንቀሳቀስ ከ568 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል። 

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን በመጠቆም። 

ገቢው የተገኘው ከደብዳቤ፣ ከጥቅልና ኢ ኤም ኤስ፣ ከሎጂስቲክስ እንዲሁም ከትራንስፖርት አገልግሎቶች መሆኑንም ነው ያስረዱት።

አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ከመልዕክት ደህንነትና ፍጥነት ጋር በተገናኘ ይገጥመው የነበረውን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻሉ ገቢውም በዛው ልክ ሊጨምር መቻሉን ተናግረዋል። 

በዚህም በበጀት ዓመቱ ያለፉት 6 ወራት 146 ሚሊየን ብር ከታክስ በፊት ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።  

ተቋሙ ከዓመታት በፊት የነበረበትን የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት የሰራው ሥራ ለውጤቱ መገኘት የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው አክለዋል። 

በተለይም የተቋሙ የፋይናንስ ቁጥጥሩ የላላ መሆኑና ወጪውን በአግባቡ አለመመዝገብ መሰረታዊ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።  

አሁን ላይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የፋይናንስ ኦዲት ክፍሉን በማጠናከርና በወጪ አወጣጥ ሂደት ላይ ያለውን ቁጥጥር ማጥበቅ በመቻሉ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ነው የገለጹት። 

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ700 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ላለፉት 129 ዓመታት ዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት በመስጠት ታሪክ ያለው አንጋፋ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም