የስንዴ ምርትን ዘመናዊ ግብይት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል

392

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስንዴ ምርትን ዘመናዊ ግብይት ለመጀመር የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን አስታወቀ።

የስንዴ ምርት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እንዲከናወን የተዘጋጀው የምርት ውል በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን የምርት ገበያ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እራሷን ለመቻል ከፍተኛ ትኩረት ከሰጠቻቸው ሰብሎች መካከል አንዱ ስንዴ ነው።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ15 ዓመት በፊት ምርቶችን ማገበያየት የጀመረው በበቆሎና ስንዴ ቢሆንም የስንዴ ምርታማነት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ከወራቶች ያለፈ ዕድሜ እንዳልነበረው አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት በስንዴ ምርት ላይ ክረምት ከበጋ እያከናወነ ያለው ተግባር ምርትና ምርታማነቱን እያሳደገው በመምጣቱና የምርቱ የገበያ መዳረሻ እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መምራት አስፈላጊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙንኬሽን ስራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ፤ የስንዴ ምርትን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአት ለማካተት የምርት ገበያ ውል በማዘጋጀት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አማካኝት ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም ማስፀደቁን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም መሰረት ምርት ገበያው የስንዴ ምርትን ወደ ግብይት ስርዓቱ በማካተት ግብይቱን ለመጀመር የሚያስችል አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ግብጦ፣ ኮረሪማ ባቄላና የሩዝ ምርቶች በግብይት ስርዓቱ ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል። 

 የስንዴ ምርትን ወደ ግብይት ስርአቱ የመግባት ሂደት ተከትሎ ስንዴ በሰፊው ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ናሙና በመውሰድ አስፈላጊው ጥናት መድረጉን ተናግረዋል፡፡ 

 በቀጣይ ምርት ገበያው ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአት ለማስገባት የሚያስችሉ ስራዎችን የሚያከናውን መሆኑንም ገልጸዋል።

የስንዴ ምርት ወደ ግብይት ስርአት እንዲገባ መደረጉ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የግብይት ስርአቶችን ለማዘመን እና አርሶ አደሮች ለምርታቸው የሚገባቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ያግዛል ሲሉ አብራርተዋል።

የምርት ገበያው ከአርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ምርት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የገለጹት የኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጁ የምርቶች ግብይቶችን በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 25 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቅርንጫፎች የሚፈፀም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አሁን ላይ በምርት ገበያው የሚገበያዩ ምርቶች ብዛት 22 መሆናቸውን ከተቋሙ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም