በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ዳያስፖራው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ

141

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ላይ ዳያስፖራው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር በውጭ ቆይተው ወደ አገር የተመለሱና አሁንም በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን ያገናኘበት መርሃ-ግብር አካሂዷል። 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ፤ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

ባለፉት አራት ዓመታት ዳያስፖራው ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ማዋሉን አስታውሰው በቀጣይ ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ማድረግ አለበት ብለዋል። 

የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም በተደረገው ርብርብ በተለይም ለኮቪድ-19፣ ለተፈናቀሉ ወገኖችና በጎ አድራጎት ሥራዎችን በመደገፍ ዳያስፖራው የላቀ ድርሻ ነበረው ብለዋል። 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብና ገበታ ለሀገር የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ድጋፍ በማድርግ የዳያስፖራው አሻራ ስለመኖሩ አስታውሰዋል። 

ባለፉት አራት ዓመታት ዳያስፖራው ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ ወደ አገር ቤት የላከ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋልም ብለዋል። 

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን በመመከት ረገድ ዳያስፖራው ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት መወጣቱንም በዚሁ ጊዜ አንስተዋል። 

በቀጣይ የዳያስፖራው ሁለንተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ ወደ አዲስ ምእራፍ ሊሸጋገር እንደሚገባም ነው ያብራሩት። 

ዳያስፖራው ለአገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰው በዚህ ረገድ የዳያስፖራ ማህበር አደረጃጀቶች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ፤ ማህበሩ ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከፖሊሲና አሰራር ጋር በተያያዘ ችግሮች እንዳይገጥሙት የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ መዋእለ ነዋይ ለማፍሰስ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ማህበሩ መረጃ ለዳያስፖራው ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

ማህበሩ aa diaspora.org የተሰኘ ድረ-ገጽ መክፈቱን የገለጸው አርቲስት ዘለቀ፤ ድረ-ገጹ ዳያስፖራው መሰማራት የሚፈልግበት ዘርፍ እንዲሁም ሕጎችና መመሪያዎች ዙሪያ መረጃ የያዘ መሆኑንም አብራርቷል። 

የውጭ ምንዛሬ ችግር እንዲፈታ ማህበሩ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነም አስረድቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም