የጀጎል ግንብን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

170

ሐረር (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የጀጎል ግንብን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ- መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጀጎል ግንብ ዙሪያ በ 6 ሺህ 114 ካሬ ሜትር ላይ የተሰራውን የአረንጓዴ ልማት ስራ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል፡፡

በዚሀ ወቅት ርዕሰ-መስተዳድሩ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ ባለፉት ዓመታት በህገ-ወጥ ግንባታና በውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ አደጋ ተጋርጦበት ነበር፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሚቴ አዋቅሮ ቅርሱን ጠብቆ ለማቆየት በወሰደው እርምጃ ቅርሱን መታደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የቅርሱ ዙሪያ ቆሻሻ መጣያ እስከ መሆን ደርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኦርዲን የክልሉ መንግስት በወሰደው እርምጃ ለወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮበትና ለጎብኚዎችና ለነዋሪው ምቹ እንዲሆን በማድረግ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

በጀጎል ግንብ ዙሪያ የተጀመረውን የጽዳትና አረንጓዴ ልማት ስራ በግንቡ ውስጣዊ ክፍልም ሆነ በከተማው ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የተጀመረውን የቅርስ ጥበቃ ስራ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና መላው ህብረተሰብ ተረባርበው እንዲያስቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሃላፊ አቶ እስማኢል ዩሱፍ በበኩላቸው በጀጎል ግንብ ዙሪያ የተተከሉ አረንጓዴ ተክሎች የከተማውን የአየር ንብረት ለውጥ ከማስተካከል አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ ልማት ስራው በ 6ሺህ 114 ካሬ ሜትር ላይ መሰራቱን የገለፁት ሃላፊው ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ለማድረግም በቀጣይም በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም