ኢትዮጵያ ከኖርዲክ ሀገራት ጋር የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራች ነው- አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ

136

አዲስ አበባ(ኢዜአ)ጥር 24/2015 ኢትዮጵያ ከኖርዲክ ሀገራት ጋር የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን በኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ ገለጹ።

በኖርዲክ ሀገራት የኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፊንላንድና ዴንማርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ፤ ኢትዮጵያ ከኖርዲክ አገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አምባሳደሩ እንዳሉት የኖርዲክ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የኖርዲክ አገራት የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ግንኙነት እያደገ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የግሉ ዘርፍ በየሀገራቱ የሚገኙ የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የማግባባት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኖርዲክ ሀገራት ጋር የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስክ ያሏትን የመዳረሻ ሥፍራዎች በአገራቱ ዘንድ በስፋት እንዲታወቁ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ የልማትና የኢኮኖሚ ትብብሯን እያጠናከረች መሆኑንም ተናግረዋል።

በኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያን ቱሪዝም በማስተዋወቅ እየተሳተፉ ያሉ የቱር ኦፕሬተሮች ለኖርዲክ ሀገራት ዘርፉን ማስተዋወቅ ለዘርፉ ልማትና እድገት የላቀ ሚና የሚኖረው መሆኑን ገልጸዋል።

የቱሪዝም አስጎብኚና የአፍሮ ፕያቶስ የጉዞ ወኪል ባለቤት ሀሚድ ካሳዬ፤ በሀገራቱ የተጀመረውን የቱሪዝም ዘርፍ የማስተዋወቅ ሥራ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል።

የኖርዲክ ሀገራት ቀጣና ለኢትዮጵያ የቱሪዝም መስክ አዲስ በር የሚከፍት እንደሚሆንና የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኛ መንገድ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ከታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት የጉዞ ወኪል ናሆም አድማሱ፤ በቅርቡ በኖርዌይና ፊንላንድ ላይ በተካሄደ የቱሪዝም ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያ ተሳትፎ ያደረገች መሆኑን ጠቁመው፤ መልካም የሚባል ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በሀገራቱ አካባቢ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በማስፋት ሰፊ የገቢ ምንጭ ማስገኘት የሚቻልበት ዕድል ይኖራል ነው ያሉት።

የኖርዲክ ሀገራት ኖርዌይን ጨምሮ በኢትዮጵያ የትምህርት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ልማትና ሌሎችንም የልማት ክንውኖች በመደገፍ ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም