በበጀት ዓመቱ ቀጣይ ስድስት ወራት በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል- ሚኒስትሮች

146

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 በበጀት ዓመቱ ቀጣይ ስድስት ወራት በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ሚኒስትሮች ተናገሩ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሐላላ ኬላ መካሄዱ ይታወቃል፡፡  

በመድረኩም በዘንድሮው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚያድግ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም ማመላከቱ ተገልጿል፡፡ 

በዘርፎች አፈጻጸም ደረጃም ግብርና፣ ኢንዱስትሪ የአገር ውስጥ ገቢ ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የግብርና ዘርፍ የ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን፤ አምራች ዘርፉም የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም የ8 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ነው በመድረኩ የተነሳው፡፡

ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 222 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገቢ መገኘቱም በመድረኩ ከቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ ያለፉት ሰድስት ወራት አፈጻጸም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጫናዎችን ተቋቁሞ እድገት በማስመዝገብ እየቀጠለ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

የአገር ውስጥ ገቢን ለማሻሻል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተሻለ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ የኑሮ ውድነቱ አሁንም በማክሮ ኢኮኖሚ እድገቱ ላይ በአሉታዊነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተለይ የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች አሁን ላይ ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

May be an image of 1 person, sunglasses and sky

በግብርናው በአምራች ዘርፍ ላይ የተከናወኑ ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የአገር ውስጥ ገቢ በ28 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን የተናገሩት ደግሞ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ናቸው፡፡

አፈጻጸሙም ከተቀመጠው ዕቅድ አንጻር 97 በመቶ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ነገር ግን ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ አሁንም የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ችግሩን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

May be an image of 1 person, standing, headscarf and outdoors

ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ አፈጻጻም ቢመዘገብም የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ከመፍታት አንጻር አሁንም ይበልጥ መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም ሚኒስትሮቹ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ የኢትዮጵያን የእዳ ጫና ለማቃለልና የወጪ ንግዱን ለማሻሻል እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፡፡

በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ላይ ጫና እየፈጠረ የሚገኘውን የዋጋ ንረት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም