የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የአዳማ አዋሽ መንገድ ጥገና የውል ስምምነት ላይ አስቸኳይ እልባት እንዲሰጥ ማሳሰቢያ ተሰጠው

400

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የአዳማ አዋሽ መንገድ ጥገና የውል ስምምነት ላይ አስቸኳይ እልባት እንዲሰጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው "ያልተገባ ውል ባለው" ስምምነት ኮርፖሬሽኑን ለእዳ የዳረጉ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የሕግ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጠይቋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2013 እና 2014 ዓ.ም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።

ኮርፖሬሽኑ "ከደንበኞች በውል የተረከባቸውን ፕሮጀክቶች ውል በተገባበት ጊዜ ገደብ የማይፈጸሙ መሆናቸው" በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአዋጅ ወደ ሌሎች የመንግስት ተቋማት እንዲተላለፉ የተወሰኑ ሃብቶች ግምትና ዕዳ ያልተገመተና በውሳኔው መሰረት ርክክብ እንዳልተደረገም ይገልጻል።

ኮርፖሬሽኑ ኮንትራት ወስዶ ለሰራቸው ስራዎቹ በአጠቃላይ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡም ተጠቁሟል።

በኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ግንባታቸው የሚጠናቀቅ መሆኑ ቢቀመጥም ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው መሰረት ያልተከናወኑ ናቸው ይላል ሪፖርቱ።

ከግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዳማ አዋሽ መንገድ ጥገና እና መንገዱን ለማስተዳደር ስምምነት ገብቶ እየሰራ ቢሆንም በውሉ መሰረት ሥራውን ባለማከናወኑ ለበርካታ ዕዳ መጋለጡ ነው የተነገረው።

ከዚህም አልፎ ኮርፖሬሽኑ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ከአሰሪ ተቋም ክፍያ መሰብሰብ አልቻለም ተብሏል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በኮንትራት አስተዳደር ላይ የተፈረመው ውል "ሰፊ ክፍተት ያለበት እና ግድየለሽነት የታየበት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"ስምምነቱ ከውጭ አገራት ድርጅት ጋር የተፈረመ ቢሆን ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችል ነበር" ብለዋል።

"በውል ስምምነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ችግር አሁንም አልተፈታም" ያሉት ዋና ኦዲተሯ የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ጥብቅ የሆነ ክትትል ማድረግ እና ችግሮች ሲፈጠሩ አፈጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት አመልክተዋል።

በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች ውል ከመገባቱ በፊት ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

"ተቋሙ እገዛ ቢደረግለት ተወዳዳሪ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል" የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው ዋና ኦዲተሯ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ ተቋሙ በ2010 ዓ.ም "በኪሳራ ውስጥ የነበረ ተቋም" ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተቋሙ ያሉት ችግሮች ሲጓተቱ የመጡ መሆናቸውንና "ስምምነቶቹ አሁን ያለው አመራር ሳይመጣ የተፈረሙ ናቸው ማሻሻያ እንዲደረግባቸው እየጠየቅን ነው" ብለዋል።

አሁን ላይ ችግሮች በመፈታት ላይ ናቸው፤ክፍያን በተመለከተም አብዛኞቹ ክፍያዎች እየተከፈሉ እንደሚገኙና ክፍያ ያልፈጸሙ አካላትን በሕግ በመጠየቅ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የአዳማ አዋሽ መንገድ ጥገናና መንገዱን ለማስተዳደር የተደረገው ስምምነት ውሉ ችግሮች የነበሩበት ስለመሆኑ አብራርተዋል።

አሁንም ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ተቋሙ ለትርፍ የተቋቋመ የልማት ድርጅት መሆኑን መገንዘብ እና ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት የአዋጭነት ጥናት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እስከ ጥር 30 2015 ዓ.ም ድረስ የኦዲት ማሻሻያ መርሐግብር ሪፖርት እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

በቀጣይ የሚደረጉ ውሎች ከመፈረማቸው በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል እንዲታዩና አሁንም እንደ ችግር እየታየ ያለው የአዳማ አዋሽ መንገድ ጥገና ውል አስቸኳይ እልባት መሰጠት አለበት ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያልሰበሰባቸው ገንዘቦችም በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ እንዲሰበሰቡ፣ ለአሰባሰቡ መጓተት ምክንያት የሆኑ የሥራ ኃላፊዎችም ተጠያቂ እንዲሆኑና የተጠያቂነት ሪፖርቱ በሶስት ወር ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ቋሚ ኮሚቴው የሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ በመቀበል በቀጣይ የእርምት እርምጃዎች እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም